ከታሪክ ጋር የተሣሠረው የጎንደር ከተማ “መሶብ” የአንድ ማዕከል አገልግሎት!

10
🏢
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር የሕዝብን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር የሚቀርፍ፤ በአንድ ማዕከል አገልግሎት ማግኘት የሚያስችል የመሶብ አንድ ማዕከል ግንባታን አጠናቋል።
የማዕከሉ መገንባት ነዋሪዎች አገልግሎት ለማግኘት ይደርስባቸው የነበረን እንግልት የሚያስቀር መኾኑን የከተማዋ ነዋሪዎች ለአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ተናግረዋል።
ማዕከሉ ከታሪካዊው የፋሲል አብያተ መንግሥታት እና ከጃንተከል ዋርካ ሥር የተገነባ በመኾኑ ማኅበረሰቡ ታሪኩን እየተመለከተ አገልግሎት እንዲያገኝ የሚያስች ነው ብለዋል። ማዕከሉ ታሪክን ከአገልግሎት ጋር ያሥተሣሠረ መኾኑንም አንሥተዋል።
የተገልጋይን እንግልት እና ብልሹ አሠራርን የሚያስቀር እና ቀልጣፋ አገልግሎትን የሚፈጥር በቴክኖሎጅ የታገዘ አገልግሎት እንዲሰጥ የሚያስችል ነው ብለዋል።
ማዕከሉ ሙሉ በሙሉ ሥራ ሲጀምር ለሕዝብ እፎይታ የሚሰጥ እንደሚኾንም ተስፋቸውን ገልጸዋል። ጎንደር በኮሪደር ልማት እና በቅርሶች እድሳት እያሳየች ያለችውን መነቃቃት የመሶብ አንድ ማዕከል ይበልጥ እንደሚያሳልጠው ተስፋ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ሲቪል ሠርቪስ እና የሰው ኃብት ልማት መምሪያ ኀላፊ ነጻነት መንግሥቴ የከተማዋ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ግንባታ ሥራ ተጠናቆ የሙከራ አገልግሎት መስጠት መጀመሩንም ገልጸዋል።
🏢 ማዕከሉን ምን ልዩ ያደርገዋል?
✅ በፋሲል አብያተ መንግሥታት እና በጃንተከል ዋርካ ሥር የተገነባ መኾኑ ተገልጋዮች ቀልጣፋ አገልግሎት እያገኙ ታሪካዊ ቅርሶችን እንዲጎበኙ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል።
የቱሪዝም መነቃቃትን እንደሚፈጥርም ጠቁመዋል። በቴክኖሎጂ የታገዘ በመኾኑ የሰነድ መጥፋትን እና ብልሹ አሠራርን ያስቀራል ነው ያሉት።
🏢 አሁን ላይ የማዕከሉ አገልግሎት የመስጠት አቅም፦
ማዕከሉ አሁን ላይ ዘጠኝ የከተማ አሥተዳደር እና ሦስት የፌዴራል ተቋማትን በመያዝ 72 አገልግሎቶችን እየሰጠ ይገኛል።
በማዕከሉ ንግድ እና ገበያ ልማት፤ ገቢዎች እና ሌሎች መምሪያ ተቋማት ቀልጣፋ አገልግሎት እየሰጡ ነው ብለዋል። በማዕከሉ በሙከራ አገልግሎት ከ1 ሺህ በላይ የማኅበረሰብ ክፍሎች አገልግሎት ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
ማኅበረሰቡ አገልግሎት ለማግኘት የሚደርስበትን እንግልት የሚያስቀር፤ ፈጣን እና ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል፤ ወጭ፣ ጊዜ እና ጉልበትን የሚቆጥብ፤ ለሕዝብ እፎይታ የሚሰጥ መኾኑንም ጠቁመዋል።
ዲጂታል ያልኾኑ ተቋማትን ዲጂታል በማድረግ ወደ ሥራ እንዲገቡ እየተሠራ መኾኑንም ጠቁመዋል።
የማዕከሉ ግንባታ ጥቅምት 2018 ዓ.ም የተጀመረ ሲኾን ቀደም ሲል የነበረን ሕንጻ በማፍረስ በአዲስ መልክ የተገነባ መኾኑም ተገልጿል።
✍️ ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleበአዲስ አበባ ዘመናዊ ተርሚናሎች በመገንባታቸው የትራፊክ አደጋን 25 በመቶ ቀንሷል።
Next article” አለማለፍ” የማይታወቅበት የደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት