
የአማራ ክልል የ2019 በጀት ዓመት የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምዝገባ ከነሐሴ18/2018 ዓ.ም ጀምሮ እየተከናወነ ይገኛል።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ደግሰው መለሰ ከአሚኮ ጋር ባደረጉት ቆይታ አዲሱን የትምህርት ዘመን በተሳካ ሁኔታ ለማስጀመር ሰፊ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውንም ተናግረዋል።
በቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ ከተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት መካከል የትምህርት ቤቶች እድሳት እና ግንባታ ሥራን ጠቅሰዋል። በዚህም ከ11 ሺህ በላይ የመማሪያ ክፍሎች መጠገናቸውን ነው የገለጹት። ከ1 ሺህ 900 በላይ አዳዲስ የመማሪያ ክፍሎች ተገንብተዋልም ብለዋል።
“አንድ ደርዘን ለአንድ ተማሪ” ንቅናቄ ሌላው የተከናወነ ዋና ተግባር መኾኑን ነው የተናገሩት። አቅም የሌላቸው ተማሪዎች በትምህርት ቁሳቁስ እጥረት እንዳይቀሩ በተደረገ ንቅናቄ እስከ አሁን ከ390 ሺህ በላይ ደርዘን ደብተሮች መሠብሠባቸውን ኀላፊው ገልጸዋል።
የሙከራ ምዝገባ ውጤት ሌላው በቅድመ ዝግጅት የተሠራ ዋና ተግባር ነው ብለዋል። ነሐሴ 14 እና 15 /2018 ዓ.ም በተካሄደ የሙከራ ምዝገባ በ158 ወረዳዎች በሚገኙ 541 ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ ተማሪዎችን መመዝገብ የተቻለበት ሁኔታ እንደነበርም አንስተዋል።
በዚህ የትምህርት ዘመን በክልሉ 7 ነጥብ 6 ሚሊዮን ተማሪዎችን ለመመዝገብ የታቀደ መኾኑንም ገልጸዋል። በምዝገባው ሂደት ወላጆች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና አጠቃላይ ማኅበረሰቡ ንቁ ተሳትፎ እያደረገ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
በቀጣይ አንድም የትምህርት ቀን መባከን እንደሌለበት ያመላከቱት ኀላፊው የምዝገባ ሂደቱ በአጭር ጊዜ ተጠናቅቆ መስከረም 05/2019 ዓ.ም የመማር ማስተማር ሥራ በይፋ እንደሚጀመር አረጋግጠዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
