
76ኛው የዓለም የጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣናዊ ኮሚቴ ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል፡፡
በጉባኤው ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የኢፊዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ዛሬ የሚደረስባቸው ውሳኔዎች በአፍሪካ ዘላቂ ችግሮችን የሚቋቋም ጠንካራ የጤና ሥርዓት ለመገንባት ያስችላሉ ብለዋል፡፡
አፍሪካ የጤና ሥርዓትን ማጠናከር እና ቀጣናዊ ትብብርን በማምጣት ተላላፊ እና ተላላፊ ያልኾኑ በሽታዎችን ለመከላከል፣ የወረርሽኝ ስጋቶችን ለመቋቋም እና የሕክምና ቁሳቁሶችን በራስ አቅም ለማምረት የጋራ ጥረት እንድታደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣናዊ ጉባኤን ማስተናገዷ ለሕዝቧ ጤና እና ለጠቅላላው የአፍሪካ ቀጣናዊ የጤና ትብብር ያላትን ጠንካራ ቁርጠኝነት የሚያሳይ እንደኾነም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በተለይም በመጀመሪያ ደረጃ የጤና ክብካቤ ማዕከላትን ማሳደግ ላይ ሰፊ ኢንቨስትመንት እያደረገች እንደምትገኝ የጠቆሙት ፕሬዝዳንቱ በአየር ንብረት ለውጥ የሚመጡ የጤና ስጋቶችን ለመቋቋም ኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ተግባርን በሰፊው እየሠራችበት እንደምትገኝ ተናግረዋል።
በዚህ መርሐግብር ሚሊዮኖችን በማሳተፍ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች መተከላቸውንም አንስተዋል።
ኢትዮጵያም ለብሔራዊ ኢንቨስትመንት፣ ለቀጣናዊ ትብብር እና ለአህጉራዊ ተቋማት በምታደርገው ድጋፍ የራሷን ድርሻ ለመወጣት ዝግጁ መኾኗን ተናግረዋል፡፡
#አሚኮ #የአየርንብረትለውጥ #ኢትዮጵያ 🇪🇹
#አዲስ_አበባ #ነሐሴ_19_2018_ዓ_ም
ዘጋቢ:- መሰረት መቅጫ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
