
1ሺህ 501ኛውን የነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የመውሊድ በዓል በደብረ ታቦር ከተማ ተከብሯል።
የደብረታቦር ከተማ እስልምና ጉዳዮች ምክርት ቤት ምክትል ሰብሳቢ ሼህ ማሕመድ ጣሂር መውሊድ የነብዩ መሐመድን (ሰ.ዐ.ወ) የሰላም እና የዕዝነት መልዕክት የምናስታውስበት፣ የአብሮነት እና የሃይማኖት መከባበር የሚጠናከርበት ታላቅ በዓል መኾኑን ገልጸዋል።
ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ለዓለማት ዕዝነት እና መከባበር ተምሳሌት በመኾናቸው በዓሉ በየዓመቱ በድምቀት እንደሚከበር ተናግረዋል።
ወጣት መሐመድ ሰይድ ወጣቶች ከበዓሉ አከባበር አስቀድሞ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶችን ለመስጠት ሲዘጋጁ መቆየታቸውን ገልጿል። የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት እና ማዕድ በማጋራት ማክበራቸውን ተናግሯል።
በዓሉ ከሌሎች የሃይማኖት ተከታዮች ጋር በፍቅር እና በመተባበር በአንድነት መከበሩንም አብራርቷል።
ወይዘሮ ወርቄ አብደላ በዓሉ ፍቅርን እና መተሳሰብን የሚያስተምር መኾኑን ገልጸዋል። ሀገር ሰላም እንድትኾን ዱዓ እያደረጉ መኾናቸውን ተናግረዋል።
በዓሉ ከሕጻናት እስከ አዋቂዎች በመንዙማ እና በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሁነቶች በድምቀት ነው የተከበረው። የበዓሉ የሰላም እና የፍቅር ምሳሌነቱ ወደፊትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተመላክቷል።
#አሚኮ #መውሊድ #ደብረታቦር #አማራክልል #ኢትዮጵያ 🇪🇹
#ደብረታቦር #ነሐሴ_19_2018_ዓ_ም
ዘጋቢ፦ ተክለብርሃን ፈንታ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
