
ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደር ጋር በመተባበር በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ5ኛ ዙር በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ ለተመረጡ የሳይበር ታለንት ተማሪዎች ሥልጠና እየሰጠ ነው።
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጅ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ምትኩ ዳምጤ (ዶ.ር) ሥልጠናው ተሰጥኦ ያላቸውን ተማሪዎች የሶፍትዌር አቅም እና የሳይበር ክህሎታቸውን ለማሳደግ የሚሠጥ መኾኑን ጠቁመዋል።
የ2030 የዲጂታል ኢኒሸቲቭ ዕቅድን እውን ለማድረግ በሳይበር ደኅንነት የሠለጠነ የሰው ኃይል ለመፍጠር ዩኒቨርሲቲው እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል። በሁለተኛ ዙር ሥልጠና 80 ወጣቶች እየሠለጠኑ ነው ብለዋል።
የአማራ ክልል ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጅ ቢሮ ምክትል ኀላፊ የቻለ ይግዛው በክልሉ አገልግሎቶች በቴክኖሎጅ የታገዙ እና ዲጂታል እንዲኾኑ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል። በክልሉ በባሕር ዳር እና በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የሳይበር ደኅንነት ሥልጠና እየተሰጠ መኾኑን ገልጸዋል።
በቀጣይ በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ለማስጀመር ይሠራል ነው ያሉት።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደር የሳይበር ልህቀት ማዕከል ዳይሬክተር ቢሻው በየነ ተቋማቸው የሀገሪቱን የኢንፎርሜሽን መሠረተ ልማት መጠበቅ፤ የሳይበር ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ እና ሌሎች ተግባራት ላይ ዓላማ አድርጎ እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
ከተለዋዋጭ የዓለም ቴክኖሎጅ ጋር አብሮ መጓዝ የሚችል አዕምሮ እና አቅም ያለው ወጣትን ለመፍጠር እየተሠራ ነው ብለዋል። ሥልጠናው በስድስት ዩኒቨርሲቲዎች እና በኢንሳ ማዕከል እየተሠጠ መኾኑን ጠቁመዋል።
በአዕምሮ፤ በአካል፤ በሥነ ልቦና የሠለጠነ እና የዳበረ ትውልድን ለመፍጠር እየተሠራ እንደኾነም ገልጸዋል። ሠልጣኞች በብቃታቸው በትላልቅ ተቋማት ተቀጥረው ውጤታማ እንዲኾኑ እና የራሳቸውን የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ የሚያስችል ነው ብለዋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሀኒባል ለማ ወጣቶች እምቅ ኃይልን የያዙ፤ አዳዲስ ነገሮችን የሚያፈልቁ፤ አዲስ አሥተሳሰብ እና ተሞክሮ ለመቀበል ፈጣን በመኾናቸው ወጣቶች ላይ ትኩረት መደረጉን ተናግረዋል።
የሥልጠናው ተሳታፊዎች ሥልጠናው ስለ ሳይበር ድኅንነት እውቅና እንዲኖራቸው፤ ክህሎታቸውን እንዲያሳድጉ፤ ስብዕናቸውን እንዲገነቡ፤ ቴክኖሎጅን ይበልጥ እንዲያውቁ ዕድል እንደፈጠረላቸው አንስተዋል።
በቀጣይ በሳይበር ደኅንነት እና በቴክኖሎጅው ዘርፍ ውጤታማ በመኾን ሀገራቸውን ለማገልገል ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
#አሚኮ #የሳይበር_ደኅንነት #ኢትዮጵያ🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ነሐሴ_19_2018_ዓ_ም
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
