ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የመሰከሩላት የፍትሕ ሀገር፦ ኢትዮጵያ

5
🇪🇹✨
በእስልምና ታሪክ ከሃይማኖታዊ ትርጉም ባለፈ በዓለም ታሪክ ለሰው ልጆች መብት፣ ለዲፕሎማሲ እና ለፍትሕ ትልቅ ምስክር የኾነ አንድ ታሪክ አለ። እሱም የኢትዮጵያ እና የነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ጥልቅ ትስስር ነው።
በዚያ ዘመን የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች በመካ ከተማ እጅግ የበረታ ስቃይ እና መከራ ይደርስባቸው እንደነበር ይነገራል። በወቅቱ የሃይማኖቱ ተከታዮች ከስቃይ እና ከመከራ ለመራቅ መጠለያ ያገኙ ዘንድ ነብዩ መሐመድን (ሰ.ዐ.ወ) ወደ ኢትዮጵያ ላኳቸው።
የባሕር ዳር ከተማ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ሠብሣቢ ሼህ መሐመድ ሰኢድ ነብዩ መሐመድ እና አስልምና፤ እስልምና እና ኢትዮጵያ (ሐበሻ) ያላቸውን ከፍተኛ ትስስር የተለዬ የሚያደርጉ ጉዳዮች እንዳሉ ያነሳሉ።
ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በተወለዱበት አካባቢ የነበሩ ተከታዮቻቸው እንዳይንገላቱባቸው ለማድረግ ኢትዮጵያን ከሀገራት ሁሉ ቅድሚያ ሰጥተው እንደመረጧት ተናግረዋል።
“ኢትዮጵያ መጠጊያ ትኾነናለች፤ በዚያ ለተከታዮቼ ማረፊያ እና መጠጊያ ቦታ አለ፤ እኔም ጌታዬ ከፈቀደልኝ ወደዚያ ብሄድ ደስ ይለኛል” እስከማለት ደረስ የተመኟት ሀገር ስለኾነች ትስስራቸው ከፍተኛ ነው ብለዋል።
ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ተከታዮቻቸውን ወደ ኢትዮጵያ መጥተው እስልምናን በሰላም እንዲያስቀጥሉ “ሂዱ ወደ ሐበሻ ምድር፣ ሐበሻ ላይ እውነተኛ፣ ታማኝ እና ፍትሐዊ ንጉሥ አለ፣ መሬቷም የእውነት መሬት የኾነች” በማለት በመንፈሳዊ ንግግር መልዕክት እንዳስተላለፉላቸው አንስተዋል።
ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በደስታም ኾነ በመከራ ጊዜ “ሐበሾችን እስካልነኳችሁ ድረስ እንዳትነኳቸው” ብለውም ጽኑ ቃል እንዳስቀመጡ ገልጸዋል።
የሃይማኖቱ ተከታይ በአጠቃላይ ትውልዱ የነብዩ መሐመድን (ሰ.ዐ.ወ) ሥነ መለኮታዊ ንግግር፣ አጠቃላይ ምግባራቸውን እና ተግባራቸውን አቅልሎ ማየት እንደሌለበት አጽንኦት ሰጥተዋል። ነብያችን እንዳከበሯት እኛም ኢትዮጵያን ማክበር አለብን ነው ያሉት።
ሼህ መሐመድ ስለ ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) አስተምህሮ ሲናገሩ “እምነት ማለት ደግነት፣ ታማኝነት እና አገልጋይነት ነው” ብለዋል።
ተከታዮቻቸውም ይህን መልካም ምግባር የምንተገብረው ለማን ነው ብለው ሲጠይቋቸው “ለአላህ፣ ለአላህ መልዕክተኛ፤ ለሙዒምኖች እና ለማንኛውም ፍጡር” ብለው እንደመለሱላቸውም ጠቅሰዋል።
ከመጾም፣ ዱዓ ከማድረግ እና ከመስጠት በፊት የመጀመሪያው ንጹሕ፣ ደግ፣ ታማኝ እና አገልጋይ መኾን እንደሚገባው ነው የተናገሩት።
ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ራስ ወዳድነትን አላስተማሩም ያሉት ሼሁ ይልቁንም “ቅድሚያ ለጓደኛ ካላለ፤ ታላቁን ካላከበረ፤ ለታናሹ እስካላዘነ ድረስ እኔ በመጣሁበት መንገድ አልመጣምና ተከታይ አይደለም፤ ፈጣሪንም አላመነም” ነው ያሉት ብለዋል። ማንኛውም ሰው ይህን የነብዩ መሐመድን (ሰ.ዐ.ወ) አስተምህሮ መውሰድ እንዳለበት አስገንዝበዋል።
በነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) መንፈሳዊ ንግግር በዚያ ልክ በተገለጸች ሀገር ላይ ስንኖር በታማኝነት፣ በፍትሐዊነት እና በእውነተኛነት ሊኾን ይገባል ነው ያሉት።
ለመኾኑ ይህ ታሪካዊ የነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)
አደራ በአሁኗ ኢትዮጵያ ምን ያህል እየተተገበረ ይኾን?
ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleመውሊድ- የመተዛዘን እና የመረዳዳት በዓል
Next articleየመውሊድ በዓል በታላቁ አንዋር መስጊድ