
የነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የልደት በዓል (መውሊድ) ሲከበር ከሃይማኖታዊ ክንውኖች ባለፈ በኅብረተሰቡ ውስጥ የፍቅር እና የአብሮነት ማሰሪያ በዓል ነው።
ይህ ዕለት የሃይማኖቱ ተከታዮች በጋራ የሚያከብሩት፤ መልካም እሴቶቻቸውን የሚያድሱበት እና አብሮነታቸውን የሚያጸኑበት ታላቅ የሰላም እና የአብሮነት ምዕራፍ እንደኾነ በአስተምህሮው ይገለጻል ።
የባሕር ዳር ከተማ ሰላም በር መሥጊድ ኢማም ሼህ ሙሐመድ አብራር መውሊድ ሲታሰብ በመጀመሪያ የሚታወሰው የነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ሰላማዊ አስተምህሮ፣ ሰብዓዊነት እና የሞራል ከፍታ ነው ይላሉ።
ዕለቱ የሃይማኖቱ ተከታይ ቤተሰቦች፣ ጎረቤቶች እና ማኅበረሰቦች ተሰባስበው ችግርን በመርሳት፣ የተራቡትን በማብላት እና በመደገፍ የርህራሄ ትስስር የሚያጠናክሩበት እንደኾነም አንስተዋል።
ኢማም ሼህ መሐመድ አብራር እንደገለጹት በችግር ጊዜም ኾነ በደስታ አብሮ የመቆም ባሕል የጥንካሬ መሠረት ነው። በዓሉ ይህንን አብሮነት የሚያድስ ድልድይ መኾኑን ነው ያስረዱት። እስልምና ዘረኝነትን በፍጹም አይፈቅድም ብለዋል።
የነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ትልቁ አስተምህሮ አንድነትን እና ሰላምን ማጠናከር በመኾኑ ሁሉም ሰው በፈጣሪ ፊት እኩል መኾኑን ተገንዝቦ እርስ በርስ መረዳዳት እንደሚገባው ነው የገለጹት።
የአንድነት እና የሰላም አምባ የኾኑትን ነብዩ መሐመድን (ሰ.ዐ.ወ) መከተል ከፈጣሪ የታዘዘ እንደኾነ በአስተምሮው ተገልጿል ያሉት ሼሁ ሙስሊሙ ማኅበረሰብ ሁልጊዜም ስለ ሰላም የሚሰብክ እና ለሀገር ሰላም የሚተጋ ነው ብለዋል።
የመውሊድ በዓል ሲከበር ጥላቻን አስወግዶ በይቅር ባይነት ላይ የተመሠረተ ማኅበረሰብ በመገንባት፤ ለሀገር ሰላም እና ለሕዝብ አንድነት በጋራ ዱዓ በማድረግ ሊኾን እንደሚገባም ነው የገለጹት።
ነቢዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ለሰው ልጅ ያሳዩትን የመተዛዘን እና የመረዳዳት እሴት በመከተል በኅብረተሰቡ መካከል ወንድማማችነት እና አብሮነትን በማጎልበት ማኅበራዊ ትስስርን ማጠናከር እንደሚገባም ተናግረዋል።
በሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
