
በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ በተለየዩ ሥርዓቶች ከሚከበሩ በዓላት መካካል መውሊድ አንዱ ነው። በባሕር ዳር ከተማ ቀበሌ አራት የሰላም በር መሥኪድ ኢማም ሼህ ሙሐመድ አብራር እንደገለጹት መውሊድ ማለት የልደት ጊዜ ወይም መወለድ ማለት ነው ብለዋል።
በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ የነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የልደት መታሰቢያ በዓል በየዓመቱ በረቢዑል አወል 12ኛ ቀን ይከበራል ነው ያሉት።
ነብዩ መሐመድ የዕዝነት፣ የአንድነት፣ የሰላም፣ የፍትሕ እና የጥሩ ሥነ ምግባር ነብይ እንደኾኑ ያስረዱት ሼህ መሐመድ በዕለቱ የሕይወት ታሪካቸውን በማስተማር ማኅበረሰቡ የእሳቸውን ፈለግ እንዲከተሉ እንደሚደረግ ነው የገለጹት። ሕዝበ ሙስሊሙም የእርሳቸውን ፈለግ በመከተል ከፈጣር ጋር ያለውን ግንኙነት ማጠናከር ይገባዋል ብለዋል።
በዕለቱ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ሰላም፤ ፍቅር እና የእርስ በርስ መተሳሰብ ይሰበካል ብለዋል።
የእርሳቸውን የሰላም እና የዕዝነት አስተምህሮ መከተል ከፈጣሪ መልካም ነገር እንደሚያስገኙ ነው ያብራሩት። ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በሕይወት ዘመናቸው ለሰው ልጅ ክብር፣ ለታማኝነት፣ ለጥሩ ሥነ ምግባር እና ለፍትሕ ልዩ ትኩረት እንደሰጡ በአስተምህሮው እንደተገለጸ ነው የተናገሩት።
አጠቃላይ የእርሳቸውን የሕይወት ታሪክ እና አስተምህሮ በማስታወስ ማኅበረሰቡ ከፈጣሪ ጋር የሚተዋወቅበት እና የሰላም አምባሳደር የሚኾኑበት ሥርዓት የሚከወንበት ዕለት እንደኾነ ነው የተናገሩት።
ሌላው በእስልምና አስተምህሮው መሠረት የመውሊድ ዕለት የሌላቸውን እና ችግረኞችን ማብላት ከፍተኛ ቦታ ያለው ነው ብለዋል። በዓሉ ሲከበር ከቤተሰብ እና ከዘመድ አዝማድ ባለፈ ማኅበራዊ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች እጅን መዘርጋት እና ማኅበራዊ ትስስርን ማጠናከር የዕለት ከዕለት ተግባራችን ሊኾን እንደሚገባም ያስተምራል ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
