
ሀገራዊ ምክክሩ መጠናቀቁን ተከትሎ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት መግለጫ አውጥቷል። የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፦
የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በንቃት የተሳተፉበት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ሐምሌ 08/2018 ዓ.ም ተጀምሮ ከትናንት በስቲያ ነሐሴ 16/2018 ዓ.ም ተጠናቅቋል።
የጋራ ምክር ቤታችን እና አባል የፖለቲካ ፓርቲዎች ላለፉት በርካታ ዓመታት በሀገራችን አካታች ሀገራዊ ምክክር እንዲካሄድ ሲያደርጉት የነበረው ጥረት በመጨረሻም እውን ሆኖ ምክክሩ በመጠናቀቁ የጋራ ምክር ቤቱ እና አባል የፖለቲካ ፓርቲዎች ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶናል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምክክሩን አስመልክቶ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከተለያዩ ተቋማት እና የኅብረተሰብ ክፍሎች ሰብስቦ ባደራጃቸው ስምንት አጀንዳዎች እና 96 ንዑስ አጀንዳዎች ማለትም፦ የሀገር ግንባታ፣ የመንግስት አደረጃጀትና ቅርጽ፣ የፖለቲካ ስርዓት፣ የፖለቲካ ውክልና እና የምርጫ ስርዓት፣ የፌዴራል ከተሞች አስተዳደር፣ የሃይማኖት ጉዳዮች፣ የተቋማት ግንባታ፣ የህግ የበላይነትና ሰብዓዊ መብቶች፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም የአርሶ አደሮች እና የአርብቶ አደሮች ጉዳዮች፣ ሙስና እና መልካም አስተዳደር፣ እንዲሁም የሰላም ግንባታ በሚሉ አጀንዳዎች ላይ ሰፊ እና ጥልቅ ውይይት ተካሂዷል።
በምክክሩ ከመላ ሀገራችን አካባቢዎች የተወከሉ በድምሩ 4 ሺህ ዜጎች ተሳትፈዋል። በውይይቱ ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት እና አመራሮች፣ የሲቪክ ማህበራት ድርጅቶች ተወካዮች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የአካል ጉዳተኞች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የንግዱ ማህበረሰብ ተወካዮች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና ምሁራን፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ መምህራን፣ ጋዜጠኞች እና ሌሎች ተወካዮች ተሳትፈዋል። በምክክሩ ላይ የጋራ ምክር ቤቱ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትም ተሳትፈዋል። በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደው ይህ ሀገራዊ ምክክር እጅግ ታሪካዊ ክስተት ነው።
ሀገራዊ ምክክሩ በሀገራችን ለረጅም ዘመናት ሲንከባለሉ የቆዩ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ አለመግባባቶችን በውይይት፣ በስምምነት፣ በመደማመጥ እና በመከባበር ለመፍታት ታሪካዊ እድል ፈጥሯል። በስኬት የተጠናቀቀው ሀገራዊ ምክክር የሀሳብ ልዩነትን በጠመንጃ ሳይሆን በጠረጴዛ ዙሪያ በውይይት እና በመግባባት መፍታት እንደሚቻል ያስመሰከረ ታሪካዊ ክስተት ነው።
በሀገራዊ ምክክሩ የተለያየ ቋንቋ፣ ባህል፣ ሃይማኖት፣ የታሪክ አረዳድ፣ የፖለቲካ ፍልስፍና እና የኑሮ ዘይቤ ያላቸው ኢትዮጵያውያን ለአንድ ወር ከግማሽ ለሆነ ጊዜ እርስ በእርስ በመነጋገር እና በመግባባት ለሀገራችን ዘላቂ ሰላም እና እድገት ይበጃል ያሉትን መፍትሔ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወንድሞቻቸው እና እህቶቻቸው ጋር በጥልቀት በመምከር ሀገራዊ አንድነትን በሚያጸና መልኩ ልዩ ልዩ ምክረ ሃሳቦችን ያመነጩበት አጋጣሚ ሆኗል።
ሀገራዊ ምክክሩ የተዛቡ የታሪክ እይታዎችን በማቀናት አብዛኛውን ኢትዮጵያዊ ሊያስማሙ የሚችሉ የታሪክ አረዳዶችን እውን ለማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል ብለን እናምናለን።
በሀገር ግንባታ ዙሪያ የነበሩት እጅግ የተራራቁ እና እርስ በእርስ የሚጋጩ አመለካከቶችን ለማቀራረብ እና በቀጣይ በጠንካራ መሰረት ላይ የተመሰረተ የሀገር ግንባታ ስራችንን ለማፋጠን ያግዛል ብለን እንገነዘባለን።
በሀገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች ለጠንካራ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት የተሻለ አስተዋጽኦ ማበርከት የሚችሉበት ጠንካራ ህገ መንግስታዊ ማዕቀፍ እንዲፈጠር እና የተሻለ ነጻ እና ፍትሐዊ የምርጫ ስርዓት ተግባራዊ እንዲሆን የሚያስችሉ ምክረ ሃሳቦችን አበርክቷል ብለን እናምናለን።
የሀገራችን የፖለቲካ እና የመንግስት አደረጃጀት ስርዓቶች ያሉባቸውን መሰረታዊ ችግሮች በጥልቀት በመረዳት ችግሮቹን ለመቅረፍ የሚያስችሉ የተሻሉ የመንግስት አደረጃጀት መፍትሔዎችን ለማመንጨት አስችሏል ብለን እንወስዳለን።
በሀገራችን ለረጅም ጊዜ የሰላም እጦት ምክንያት በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ የተሻለ መግባባት ለመፍጠር ታሪካዊ እድል እንደፈጠረ እንገነዘባለን።
በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ የመፍትሔ ሃሳቦችን ከማመንጨት በላይ፣ በሀገራችን የሀሳብ ልዩነቶችን በምክክር የመፍታት አዲስ ባህል እና ተግባራዊ ልምምድ እንዲዳብር ታሪካዊ እድል ሰጥቷል ብለን እናምናለን።
ላለፉት በርካታ ዓመታት ቅድመ ዝግጅት ሲደረግበት የቆየው ሀገራዊ ምክክር መገባደዱን ተከትሎ ቀጣዩ ምዕራፍ በምክክሩ የተለዩ ምክረ ሃሳቦችን ገቢራዊ ማድረግ ይሆናል። በሀገራዊ ምክክሩ የተሰጡ ምክረ ሃሳቦች በተቻለ ፍጥነት ተግባራዊ የሚሆኑበት ሁኔታ እንዲፈጠር፣ በተለይም ጉዳዩ የሚመለከታቸው የህግ አውጪ እና አስፈጻሚ የመንግስት አካላት የሚጠበቅባቸውን እንዲያደርጉ ጥሪ እናቀርባለን።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በዛሬው ዕለት በተጠናቀቀው ሀገራዊ ምክክር የተሰጡ ምክረ ሃሳቦች በተገቢው ጊዜ እና ሁኔታ ተግባራዊ መሆን ይችሉ ዘንድ በትግበራ ሂደቱ ለሚሳተፉ አካላት አቅሙ የፈቀደውን ያህል ድጋፍ እና ትብብር ያደርጋል።
የጋራ ምክር ቤታችን እና የሀገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች የምክክሩ ምክረ ሃሳቦች ተግባራዊ እንዲሆኑ፣ በተለይም ጠንካራ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት በሀገራችን እውን እንዲሆን የሚጠበቅብንን ሁሉ የምናደርግ መሆናችንን በዚህ አጋጣሚ እየገለጽን፣ ለሀገራዊ ምክክሩ በስኬት መጠናቀቅ ሁለንተናዊ ድጋፍ ላደረጉ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት የከበረ ምስጋና እናቀርባለን።
ምክር ቤቱ በተለይም በሀገራችን ሀገራዊ ምክክር እውን እንዲሆን፣ ሃሳብ ከማመንጨት ጀምሮ በምክክሩ የዝግጅት ሂደት እንዲሁም በምክክሩ ወቅት ንቁ እና አወንታዊ ድጋፍ ላበረከቱ የምክር ቤቱ አባል የፖለቲካ ፓርቲዎች ከፍተኛ ምስጋና ያቀርባል።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት
