የሉዓላዊነታችን ህያው ጋሻ

22

ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ግርማዋ ብቻ ሳይኾን በልጆቿ ብረት በሚመስል ፅናት፣ ወሰን በሌለው ፍቅር እና መስዋዕትነት የቆመች የፅናት ተራራ ናት።

ከሰማዩ ግርማ በታች በበረሃው አሸዋና በደጋው ቁር ውስጥ የሀገርን እና የዜጎችን ደኅንነት ለመጠበቅ የሚተጉት የእነዚያ ጀግኖች ታሪክ ግን የተለመደ ወታደራዊ ብቻ አይደለም፤ የሰው ሕይወት፣ የእናት ፍቅር፣ የሀገር ፍቅር እና የመስዋዕትነት ህያው መከታ እንጂ።

የጥቁር ሕዝቦችን ታላቅ ታሪካዊ ድል ካበሰረው ዓድዋ እስከ ካራማራ አሸዋማ ምድር፣ እንዲሁም ድንበር ተሻግሮ የዓለምን ሰላም ለማስከበር በተሄደበት እያንዳንዱ እርምጃ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ታሪክ ከሀገሪቱ ህልውና ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ነው።

ዛሬ ላይ ያ ታሪካዊ ጀግንነት ይበልጥ በዘመናዊ ዕውቀትና በቴክኖሎጂ ልህቀት ተጎናፅፏል። ሠራዊቱ የውጊያ ታክቲክን ከከፍተኛ ወታደራዊ አካዳሚዎች ዕውቀት ጋር በማቀናጀት የዘመኑን ሳይንስ የታጠቀ መኮንን እያፈራ ይገኛል።

ሰው አልባ አውሮፕላኖች፣ የራዳር ሥርዓቶች እና የሳይበር ደህንነት መዋቅሮች የሀገሪቱን ሰማይና ድንበር አይደፈሬ አድርገውታል።

በሀገር ውስጥ የሚገኙ የመከላከያ ኢንዱስትሪዎች አነስተኛና መካከለኛ ተተኳሾችን እንዲሁም የታጠቁ ተሽከርካሪዎችን በራስ አቅም በማምረት የሉዓላዊነታችንን መሠረት እያጠነከሩት ይገኛሉ።

የመሬት፣ የአየር እና የኮማንዶ ኀይሎች በቅንጅት ሲንቀሳቀሱ በማንኛውም መልከዓ-ምድርና የአየር ሁኔታ ውስጥ የመብረቅ ያህል ፈጣንና ወሳኝ ምላሽ የመስጠት የተቀናጀ አቅም ገንብተዋል።

 

የኢፌዴሪ የጦር ኀይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እንደገለጹት ዛሬ ኢትዮጵያ የብሔራዊ ጥቅሟን በፅኑ መሠረት ላይ የሚያስጠብቅ ታላቅ ተቋም ገንብታለች።

በተለይም የአየር ወለድና ኮማንዶ ኀይል በአካል ብቃቱ፣ በፅናቱና በከፍተኛ ወታደራዊ ጥበቡ የውጊያን አቅጣጫ በቅጽበት የመቀየር አቅም ያለው የሀገር መከታ መሆኑን አብራርተዋል።

አስቸጋሪና ፈታኝ ሁኔታዎችን አልፎ ሀገራዊ አደራውን በብቃት የመወጣት አቅሙ ዛሬም ነገም ለሀገር ዋስትና መሆኑን አረጋግጠዋል።

ሀገር ማለት በድንበር ላይ የሚቆም ወታደር ብቻ ሳትኾን ያ ወታደር ደሙንና አጥንቱን ሰጥቶ የሚጠብቃት የሁላችንም የጋራ ቤት ናት።

#አሚኮ #Defencenews #Ethiopia
#ነሐሴ 17/2018 ዓ.ም

ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article“ሻደይ ውበታችን ነው” የሻደይ ተጫዋቾች
Next articleየአሸንድዬ በዓል በእብናት እየተከበረ ነው።