የሕገ-ወጡ ቡድን አዲስ ሴራ

46
ሕገ ወጡ የሕወሃት ቡድን ፖለቲካዊ ህልውናው በሰላም አየር ውስጥ አይደለም። ይልቁንም በትርምስና በመከራ ውስጥ መኾኑን በታሪኩ አስመስክሯል።
ሕገ ወጡ ቡድን አሁንም አዲስ ሴራ እየጠነሰሰ ይገኛል። ዓላማውም የኢትዮጵያን የመረጋጋት ተስፋ ማጨለም ነው። ቡድኑ ብቻውን ኾኖ ሀገርን መበጥበጥ እንደማይችል ተገንዝቧል። የራሱ አቅም ሲያጥርበት የሌሎችን ጽንፈኝነት እንደ ማገዶ ተጠቅሟል፣ እየተጠቀመበትም ይገኛል። በዚህም ከተለያዩ አፍራሽ ኀይሎች ጋር የጥፋት ጥምረት ፈጥሯል።
የጥምረቱ ግብ ሀገርን ወደማያባራ የእርስ በእርስ እልቂት መክተት ነው። ይህ ጥምረት በጋራ የሀገር ግንባታ ራዕይ ላይ የተመሰረተ አይደለም። ይልቁንም ኢትዮጵያን በማዳከምና በማፍረስ የጋራ ጥላቻ ላይ የተገነባ ነው።
የቡድኑን አጥፊ መንገድ መነሻ በተመለከተ አረጋዊ በርሄ (ዶ.ር) ያስረዳሉ። ሕወሃት በፌዴራል መንግሥቱ እና በሕገ መንግሥቱ መተዳደር አይፈልግም። ምክንያቱንም ላጠፋው ጥፋት ሕጋዊ ተጠያቂነት ይመጣብኛል ብሎ ክፉኛ ይፈራል በማለት ጠቁመዋል።
ሕገ ወጡ ቡድን፣ ኢትዮጵያውያን በመራባቸው ዓመታት ያካበተውን ሀብት ይዞ መቀጠል ይፈልጋል። ሕዝቡንም በበላይነት ለመበዝበዝ አስቧል። ለዚህም ተገንጥሎ የራሱን መንግሥታዊ ክልል የመፍጠር ዓላማ እንዳለው ነው የጠቆሙት። የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ሙሉ በሙሉ ከተተገበረ ይህ ሕልሙ ይከሽፋል ነው ያሉት። ስለዚህም ከሰላም ይልቅ ጦርነትን ቀዳሚ ምርጫው እንደሚያደርግ ነው የገለጹት።
ቡድኑ “ከእኔ ውጪ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር አትኖርም” የሚል የትዕቢት አቋም አለው። ከዚህ የጥቅም ስሌት በመነሳትም ጦርነቱን ወደ ሌሎች አካባቢዎች እያስፋፋ ነው። በዚህም አዲስ የትርምስ ቀጣና ለመክፈት እየሞከረ ነው። ይህ “እኔ ካልገዛኋት ትፍረስ” የሚል አውዳሚ የዜሮ ድምር ፖለቲካ ነው።
አሁናዊ የቡድኑ ድርጊት ለትግራይ እና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ያለውን ጥልቅ ንቀት ያሳያል። ሕዝቡ ከጦርነት አዙሪት ወጥቶ ማረፍና ማልማት ይፈልጋል። ቡድኑ ግን በዚህ ወሳኝ ወቅት የሕዝብን ደምና እንባ ለፖለቲካ ቁማር እየተጠቀመበት ነው። ዓላማውም የሀገሪቱን ታሪካዊና ማኅበራዊ ትስስር መበጠስ ነው። ወንድም ከወንድሙ ጋር በጥርጣሬ እንዲተያይ ማድረግንም በትኩረት እየሠራበት ነው።
አዲሱ የጥፋት ጉዞ ከባድ የህልውና ፈተና ነው። መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህንን ከመቼውም ጊዜ በላይ ነቅቶ ሊያከሽፈው ይገባል። የጥፋት ኃይሎች ሴራ የሚከሽፈው ደግሞ ጠንካራ ሀገራዊ አንድነትን በመገንባት ነው።
የታሪክ ንቀቱን እና የጥፋት ትርክቱን በማያዳግም እርምጃ በማክሸፍ ኢትዮጵያ በሴረኞች ጥምረት እንደማትፈርስ ይልቁንም በልጆቿ የጋራ ጽናት የምትጸና ሀገር መኾኗን በተግባር ማረጋገጥ ይገባል።
በስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“ከ20 ሺህ በላይ ዜጎችን የመኖሪያ ቤት ቦታ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል” አቶ ጎሹ እንዳላማው
Next article“ሻደይ ውበታችን ነው” የሻደይ ተጫዋቾች