
ቀኑ ዕለተ እሑድ፣ ሰዓቱ ደግሞ ጠዋት 3፡00 ገደማ። በባሕር ዳር ከተማ የአንድ ሰፈር ሰላማዊ ድባብ ድንገት በከባድ ጭቅጭቅ ተናወጠ። ምክንያቱ ደግሞ አዲስ ወደ ተከራዩት ቤት የቤት እቃ ጭነው የመጡ አዲስ ተከራዮች እና በአካባቢው ቀድመው ሲጠብቁ በቆዩ ሕገወጥ ጫኝ እና አውራጆች መካከል የተፈጠረ አለመግባባት ነው።
ተከራዮቹ ዕቃቸውን በራሳቸው እና በወዳጆቻቸው እርዳታ ማውረድ ቢጀምሩም፣ “ይህ የእኛ ሰፈር ነው፤ ሥራውም የኛ ድርሻ ነው፤ ያለ እኛ እጅ አንድም እቃ አይወርድም” የሚል ያልተጠበቀ የእገዳ ግድግዳ ከፊታቸው ተደቀነ። ለጥቂት ደቂቃ ተግባራቸው የጠየቁት ክፍያ ደግሞ 3 ሺህ ብር ገደማ ነበር። ተከራዮች አቅማቸው እንደማይፈቅድ እና እራሳቸው ማውረድ እንደሚፈልጉ ቢናገሩም አትችሉም በመባላቸው ነገሩ ወደ ከፋ ጭቅጭቅ አምርቷል።
በመጨረሻም የአካባቢው ሽማግሌዎች ጣልቃ ገብተው ባደረጉት ረጅም ምክር ክፍያው ወደ 1 ሺህ 500 ብር ዝቅ ብሎ ስምምነት ላይ ተደረሰ። የእቃው ባለቤቶችም ንብረታቸውን የማውረድ ብቁ ጉልበት ቢኖራቸውም ቁመው በመመልከት ለተጨማሪ ወጭ ተዳረጉ።
ይህ አጋጣሚ በከተማዋ በሕገ ወጥ ጫኝ እና አውራጆች አማካኝነት በበርካታ ግለሰቦች ላይ እየደረሰ ያለውን እንግልት በግልጽ የሚያሳይ በዚህ ሳምንት መጨረሻ የታዘብኩት ሁነት ነው። ትዝብታችን ባሕር ዳር ከተማ ላይ ይሁን እንጅ በየከተማው እንዲህ አይነት ችግሮችን የሚፈጥሩ ሕገ ወጥ ጫኝና አውራጆች እንደሚኖሩ ግን እሙን ነው።
ጉዳዩን አስመልከቶ አሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ያነጋገራቸው የባሕር ዳር ከተማ ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ዋለልኝ ቢምረው ሕጋዊ ፈቃድ ሳይኖራቸው “እኛ ብቻ ነን የምናወርደው” በማለት ነዋሪውን የሚያስቸግሩ የተደራጁ ግለሰቦች መኖራቸውን አረጋግጠዋል።
በተጨማሪም የተወሰኑ የኮሚሽን ሠራተኞች አገልግሎት ሳይሰጡ ከደረቅ ጭነት መኪኖች ላይ “በግዴታ ኮሚሽን ትከፍሉናላችሁ” በማለት ከተሰጣቸው ፈቃድ ውጭ ገንዘብ እንደሚጠይቁ ጥቆማ እንደደረሳቸውም ገልጸዋል።
ለዚህም አሁን ላይ በኮሚኒቲ ፖሊስ ኦፊሰሮች አማካኝነት ሕገወጥ ድርጊት የሚፈጽሙ ሰዎችን የመያዝ፣ የመምከር እና በሕግ እንዲጠየቁ የማድረግ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝም ኮማንደር ዋለልኝ ተናግረዋል።
ማንኛውም አካል ከተሰጠው ሕጋዊ ፈቃድ ውጭ መሥራት ሕገወጥ በመኾኑ ሁሉም ከድርጊቱ እንዲቆጠብ ያሳሰቡት መምሪያ አዛዡ፣ ኅብረተሰቡ መሰል ድርጊቶች ሲያጋጥሙት ወዲያውኑ ለጸጥታ አካላት ጥቆማ በመስጠት ከፖሊስ ጋር ተቀናጅቶ እንዲሠራም ጥሪ አቅርበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
