ኢትዮጵያ ዓለምን ያስደመመችበት የአረንጓዴ አሻራ ዲፕሎማሲ

11
በዓለም ዘንድ የድርቅ እና የርሃብ መገለጫ ተደርጋ ለዘመናት ስትቆጠር የነበረች ሀገረ በቅርብ ዓመታት እየፈጸመቻቸው በምትገኘው ስኬታማ ፕሮጀክቶች የዓለምን ትኩረት እየሳበች ትገኛለች። በራሷ አቅም ጀምራ መፈጸም እንደምትችልም አሳይታለች። የሕዳሴ ግድብን በማጠናቀቅ ዓለም ይመለከታት የነበረውን የታዛባ ዕይታ ቀርፋለች። አዲስ መልኳንም ለዓለም አስተዋውቃለች።
የተወሰኑ ሀገራት ብቻ የሚሞክሩትን የአረንጓዴ አሻራ ልማት ኢትዮጵያ ግን በትንሽ ዓመታት በልዩ ዘመቻ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርን በሚሊዮን ሕዝቦቿ በየዓመቱ በመትከል ገጽታዋን ገንብታለች። ይበልጥ የዓለምን ትኩረት የሚስበው ደግሞ ለዓመታት በአንድ ጀምበር በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል ታሪክ መሥራቷ ነው።
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በ2018 ዓ.ም በአንድ ቀን 800 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ያከናወነችው ተግባር የበርካታ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችን ትኩረት ይዞ አልፏል። የቻይና ሲጂቲኤን እና ዥንዋ ሚዲያዎች በ800 ሚሊዮን የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ የኢትዮጵያ ሕዝብ በከፍተኛ ተነሳሽነት ስሜት መሳተፉን ዘግቧል።
የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የተራቆተ መሬትን መልሶ ለማቋቋም፤ የሀገሪቱን የደን ሽፋን ለማሳደግ፤ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም፤ ብዝኃ ሕይወትን ለመጠበቅ ትኩረት ያደረገ ብሔራዊ የአካባቢ ጥበቃ መርሐ ግብር መኾኑን ዘገባዎቹ አትተዋል።
ታዋቂው ቲቪ ብሪክስ (TV BRICS) ሚዲያ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ አካባቢያዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖን በማጉላት ለኢትዮጵያ ዘላቂነት ኢንቨስትመንት እንደሚፈጥር በወቅቱ ዘግቦት ነበር። የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፤ የግብርና ምርታማነትን ለማሻሻል እና የአየር ንብረት ለውጥ የሚያመጣቸውን ተጽዕኖዎች የመቋቋም አቅምን ለማጠናከር ያለመ መኾኑንም አትቷል።
ኦል አፍሪካ በዘገባው “የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኀን ኢትዮጵያ በአንድ ቀን 800 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ያደረገችውን ታሪካዊ ዘመቻ አደነቁ” ሲል በገጹ ላይ በአርዕስት አስነብቦም ነበር።
በኤዥያ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በላቲን አሜሪካ እና በአፍሪካ ቀንድ የሚገኙ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ኢትዮጵያ ያከናወነችውን የአረንጓዴ አሻራ ልማት ማወደሳቸውን ዘገባው አካትቷል።
በሕዝብ ተሳትፎ ረገድ ትልቅ ምዕራፍ ያረፈበት ስኬት መኾኑንም አስነብቧል። ይህ የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ትኩረት ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ ዲፕሎማሲ ስኬታማ ተግባርን እያከናወነች እንደምትገኝ ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል።
ዘጋቢ፦ ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleበአማራ ክልል ስምንት ትምህርት ቤቶች ሙሉ ለሙሉ ተማሪዎቻቸውን አሳልፈዋል።
Next articleያልተጋበዙ የዕቃ አውራጆች ወከባ ሕገ ወጥ ነው።