
በሀገር መከላከያ ሠራዊት የልዩ ዘመቻዎች እዝ ማሠልጠኛ ማዕከል ያሠለጠናቸውን መሠረታዊ ኮማንዶዎች አስመርቋል።
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ጀግኖች አባቶቻችን ዘመናዊ መሣሪያ ሳይታጠቁ የሀገር ሉዓላዊነትን ጠብቀው ማቆየታቸውን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ታሪካዊ እና ወቅታዊ ጠላቶች ሀገሪቱን ለማጥፋት ለዘመናት ያደረጉት ጥረት አልተሳካላቸው ነው ያሉት።
ይህንኑ እኩይ ተግባራቸውን በመቀጠልም አሁን ላይ በእጅ አዙር የሀገር ውስጥ እና የውጭ ባንዳዎችን በመጠቀም ሀገር ለማፍረስ እየሠሩ መኾኑን ተናግረዋል። ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ምሽግ እና መከታ የኾነው የመከላከያ ሠራዊት ጠላትን እየመከተ እና እያንበረከከ ጉዞውን ቀጥሏል ነው ያሉት።
ሠራዊቱ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ግኝቶችን ተጠቅሞ እና ኪሳራን ቀንሶ በነበልባል አቅም የሚዋጋበትን አቅም ፈጥሯል ብለዋል።
ዛሬ የተመረቁ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የ45ኛ ዙር የልዩ ዘመቻ ኮማንዶ ተመራቂዎችም ለሠራዊቱ ተጨማሪ አቅም የሚኾኑ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች መኾናቸውን ተናግረዋል።
የኮማንዶ ሥልጠናን የሚወጣው ጀግና የኾነ ብቻ ነው ያሉት ፊልድ ማርሻሉ ተመራቂ ኮማንዶዎቹ ሀገር የፈጠረችላቸውን አቅም በመጠቀም ሉዓላዊነቷ የተረጋገጠ ኢትዮጵያን ለትውልድ እንዲያስቀጥሉም አደራ ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ቤተልሔም ሰለሞን
#አዲስ_አበባ #ነሐሴ_16_2018_ዓ_ም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
