“እየተመካከርን ሀገር እንገነባለን፣ ሀገር እየገነባንም እንማከራለን” ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ

15

 

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባዔ ማጠቃለያ መርሐ ግብር ተካሂዷል። በማጠቃለያ መርሐ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በደማቅ ቀለም ኢትዮጵያን ወክላችሁ ተወያይታችሁ እና ተነጋግራችሁ ለዚህ ቀን በመድረሳችሁ ምስጋና ላቀርብላችሁ እወዳለሁ ብለዋል።
ኢትዮጵያ እንድትመክር ላደረጉ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል። በኢትዮጵያዊ ታጋሽነት ምክክሩ እንዲካሄድ በማድረጋችሁ በእርግጥም የሚደነቅ ነው ብለዋል።

ምክክር በባሕላችን የቆዬ ቢኾንም የችግሮቻችን መድኅን እንዲኾን የማድረግ ድፍረት እንዳልነበር አንስተዋል።

በሀገራዊ ምክክር ጉባኤው የቀረቡ ሃሳቦች ለፖለቲካ ልምምድ እና ለሀገር ግንባታ ያላቸው ፋይዳ ትልቅ መኾኑን ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ያለውን ስጋት እና ተስፋ በመመካከር ይበጃል ያሉትን ማቅረባቸውን አንስተዋል።

ምክክሩ የሁላችንም የኾነችውን ኢትዮጵያን የሚገልጡ እና የሚያጸኑ የጋራ መሻትን፣ ርእይ እና እጣ ፋንታን በአንድ ላይ ለማራመድ የሚያስችል ዕውቀት የተንሸራሸረበት መኾኑን ገልጸዋል።

ምክክሩ የኢትዮጵያ የፖለቲካ አውድ ከተቃርኖ ወጥቶ በይቅርታ እና በስርየት ጎዳና እንዲራመድ መሠረት የጠላ ስለመሆኑም ተናግረዋል።

ከአምባጓሮ፣ ከነፍጥ እና ከአመጽ አዙሪት የፖለቲካ ልምምድ በመላቀቅ ፖለቲካው በሰላም እና በመደማመጥ እንዲመሠረት በር የከፈተ እንደኾነ ነው ያነሱት።

ኢትዮጵያ መስቀለኛ መንገድ ላይ ናት፣ ኢትዮጵያ ልትፈርስ ነው፣ ኢትዮጵያ ልትበተን ነው ያልተባለበት ጊዜ አልነበረም፣ ነገር ግን ይህ ኢትዮጵያን የማይገልጽ እንደኾነ ማረጋገጥ ያስፈልጋል ነው ያሉት። እነዚህ አገላለጾች ለኢትዮጵያ የማይኾን እና ኢትዮጵያ የማታውቃቸው ናቸው ብለዋል።

ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያ ጉዞ የሚኾነው ቀጥ ያለ፣ ርእቱ እና ብርቱ ነው ብለዋል።

ምክክሩን በትዕግሥት ለተከታተለው የኢትዮጵያ ሕዝብም ምስጋና አቅርበዋል። ሀገር የሚገነባው በፖለቲካ ውል ብቻ አይደለም፤ ሀገር የሚገነባው በማኅበራዊ ትስስር ነው ብለዋል። የቀረቡ ምክረ ሃሳቦች የቀጣይ ፍኖተ ካርታዎች መኾናቸውን አንስተዋል።

ፈተናዎቻንን በራሳችን ጥበብ ለመፍታት ውስጣችንን የፈተሽንበት የታሪክ ባለቤትነታችንን ያረጋገጥነበት ታላቅ አፍሪካዊ ክንውን ነው ብለዋል። በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ አዲስ ጎዳና መኾኑን ገልጸዋል። “እየተመካከርን ሀገር እንገነባለን፣ ሀገር እየገነባንም እንማከራለን” ነው ያሉት።

#አሚኮ #nationaldialogue #Ethiopia

Previous article“ኢትዮጵያ ልዩነቶችን በአንድነት የያዘች የብሔር ብሔረሰቦች ሀገር ናት” ኦሌሶንጎ ኦባሳንጆ
Next article“ሻደይ፣ አሸንድየ እና ሶለል የሕዝባችንን አብሮነት የሚያጠናክሩ ቅርሶቻችን ናቸው” ርእሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ