
ኢትዮጵያውያን ለፍትሕ እና ርትዕ ከፍተኛ ቦታ አላቸው። “በፍርድ ከተወሰደች በቅሎዬ ያለፍርድ የተወሰደች ጭብጦዬ” ይላሉ። በሕግ አግባብ እና በፍርድ ከተወሰደባቸው ትልቅ ነገር ይልቅ ያለ አግባብ ያለ ፍርድ የተወሰደባቸው ትንሽ ነገር ያንገበግባቸዋል። ትልቅ የፍትሕ መጓደል ስሜትም ይፈጥርባቸዋል።
ኢትዮጵያውያን ከድሮ እስከ ዛሬ በደል እንዳይፈጸም፤ የተበደለ ፍርድ እንዲያገኝ፤ የበደለ እንዲክስ፤ ሐቅ እንዲመለስ፤ ሰዎች ያለ ፍትሕ እንዳይቀሩ ያላቸው አቋም ጠንካራ ነው።
በኢትዮጵያውያን ዘንድ በትልቅ ሀብት ላይ የሚመጣን ሕጋዊ ውሳኔ በበጎ የማስተናገድ ሕዝባዊ እሴት ቢኖራቸውም መሠረታዊ በኾነ መብት ላይ የሚፈጸምን ሕገ-ወጥ ወረራ ግን የሚቀበል ሕሊና የላቸውም። ለዚያም ነው “በፍርድ ከተወሰደች በቅሎዬ ያለፍርድ የተወሰደች ጭብጦዬ” ታንገበግበኛለች የሚሉት።
አባባሉ ወደ ሀገራዊ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ እውነታ ስናመጣው ኢትዮጵያ ከባሕር በር ጋር ያላትን ታሪካዊ ግንኙነት፤ የገጠማትን ኢ-ፍትሐዊ መገለል እና የኢትዮጵያ ሕዝብን የባሕር በር ያደረ ጥያቄ በአግባቡ ይገልጻል።
ኢትዮጵያ ከጥንት ዘመን እስከ 1983 ዓ.ም ድረስ በነበራት ሰፊ የባሕር በር በንግድ እንቅስቃሴ ከዓለም ትገናኝ ነበር። በባሕር ኀይሏም የቀጣናውን ሰላም በንሥር ዐይን ትጠብቅ እንደነበር ታሪክ ይነግረናል።
ይሁን እንጂ የውጭ እና የውስጥ ኀይሎች በሠሩት ደባ እና ሴራ ከባሕር በር ባለቤትነቷ ከተገፋች ውላ አድራለች። ይህ መገለል ፍትሕን የጣሰ ታሪካዊ ሂደት ከመኾኑም በላይ በራሷ ታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ ሀብት ባይተዋር አድርጓታል።
ይህ ያለ አግባብ የተወሰደባት የባሕር በር ባለቤትነት ዛሬ ላይ በኢኮኖሚ፣ በሰላም እና ደኅንነቷ ላይ እያሳደረ ያለው ጫና ከፍተኛ ነው።
ይህ ያለአግባብ እና ኢ- ፍትሐዊ የኾነ የኢትዮጵያ ከባሕር በር መገለል በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ በቀላሉ የሚታይ አልኾነም። የሀገርን ሉዓላዊ መብት ያለ አግባብ የመንጠቅ እና ሕዝቧን ለዘላቂ ድህነት አሳልፎ የመስጠት ያህል የሚቆጠር ከፍተኛ የፍትሕ መጓደል ስሜትን ፈጥሮባቸው ቆይቷል።
እንኳንስ ያለአግባብ የተወሰደባት ኢትዮጵያ ቀርቶ የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት የባሕር በር የማግኘት ዓለም አቀፍ መብት ተሰጥቷቸዋል። ታዲያ ለመላው ጥቁር ሕዝብ የነጻነት ምሳሌ የኾነው የኢትዮጵያ ሕዝብ በራሱ ላይ የተፈጸመን ኢ- ፍትሐዊ መገለል አሜን ብሎ እንደማይቀበል ታውቆ ያደረ ነው።
ኢትዮጵያ ያለአግባብ የተነጠቀችውን ተፈጥሯዊ ሀብት በሰላማዊ፣ በሕጋዊ እና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ ተመስርታ ለመመለስ የምታደርገው ትግል ፍትሐዊ ነው።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄዋን ስታስመልስ የሰላሟ፣ የዕድገቷ እና የደኅንነቷን ማረጋገጫ ከማግኘቷም በላይ የተነጠቀችውን ፍትሕ በማስመለስ በዓለም ፊት ለፍትሕ እና ለርትዕ የምትታገል ሀገር መኾኗን ታስመሰክራለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተለያዩ ጊዜያት ባደረጉት ንግግር ቀይ ባሕር እና ኢትዮጵያ ለዘላለም ተነጣጥለው ሊኖሩ የማይችሉ ተፈጥሯዊ ቁርኝት ያላቸው መኾናቸውን ተናግረዋል።
የቀይ ባሕር የኢትዮጵያ ጥያቄ ሕጋዊ፣ ታሪካዊ፣ መልክዓ ምድራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄ መኾኑን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ቀይ ባሕርን እንዴት እንዳጣችው የሚል ሕጋዊ ማስረጃ አንድ ገጽ ወረቀት ማግኘት አልቻልንም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕጋዊ ባልኾነ መንገድ ያጣነውን ጉዳይ ማን ወሰነው ብሎ መጠየቅ ሕሊና ካለው የሚጠበቅ ነው ብለዋል።
የእኛ የኾነውን ቀይ ባሕርን መልሶ ለመጠየቅ የሚሰጋ እና የሚጠራጠር ትውልድ መፈጠሩ የሥነ ልቦና ስብራት አካል ነው ብለዋል። ኢትዮጵያን የሚያህል ሀገር ታሽጋ ለልጆቻችን ትሸጋገር ማለት ተገቢ እሳቤ አይደለም ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ የጅኦግራፊ እስረኛ ኾና ለዘላለም ትኖራለች ብሎ የሚያስብ ኢትዮጵያዊ ካለ እሱ የሞተ ነው ብለውታል። ሰላም ታስቀድማለች፤ ድህነትን ትፋለማለች፤ መውጫ መግቢያ በሯን ታበጃለች ብለዋል።
በአድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
