የአዳርቃይ ወረዳ ከ27 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተበረከተለት።

9
የኢትዮጵያ ሒሳብ አያያዝ ኦዲት ቦርድ እና የኢትዮጵያ ዕዳ እና ሀብት አሥተዳደር ኮርፖሬሽን በጋራ በሰሜን ጎንደር ዞን ለአዳርቃይ ወረዳ ከ27 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አድርገዋል።
ተቋማቱ በክረምት በጎ ፈቃድ መርሐ ግብር የአጸደ ሕጻናት ትምህርት ቤት ግንባታ፤ የአቅመ ደካማ ቤቶች ጥገና፤ የትምህርት ቁሳቁስ እና የግል ንጽሕና መጠበቂያ ግብዓቶችን ነው ድጋፍ ያደረጉት።
የኢትዮጵያ ሒሳብ አያያዝ እና ኦዲት ቦርድ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ጽዋዬ ሙሉነህ በወረዳው ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ የገንዘብ ወጭ የቅድመ አንደኛ አጸደ ሕጻናት ትምህርት ቤት ለመገንባት የሚያስችል ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
የበጎነት እና የመተባበር ሀገራዊ እሴትን ማስቀጠል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ዕዳ እና ሀብት አሥተዳደር ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር ሙሉዓለም ጌታሁን የወረዳው ማኅበረሰብ ከደረሰበት ጉዳት እንዲያገግም ለማገዝ አምስት የአቅመ ደካማ ቤቶችን ደረጃቸውን በጠበቀ መንገድ መልሶ ለመገንባት መታቀዱን ገልጸዋል።
የሰሜን ጎንደር ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የትምህርት መምሪያ ኀላፊ ክቡር አሰፋ ተቋማቱ የአጸደ ሕጻናት ግንባታ እና የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋቸው የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ በኩል ሚናው የጎላ ነው ብለዋል።
በታዳጊዎች ሥነ-ምግባር፣ ክህሎት እና ማንነት ግንባታ ላይ መሥራት በራስ መተማመን ያለው፣ ምክንያታዊ እና ችግር ፈቺ ትውልድ እንዲፈጠር ያግዛል ነው ያሉት።
የአዳርቃይ ወረዳ አሥተዳዳሪ ደሳለኝ አባተ በወረዳው ከዚህ ቀደም የአጸደ ሕጻናት ትምህርት ቤት ባለመኖሩ ሕጻናት ከትምህርት ገበታ ርቀው መቆየታቸውን ተናግረዋል።
በቀጣይ ከተቋማቱ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የሚገነባው አጸደ ሕጻናት በወረዳው ያለውን የትምህርት ቤት ሽፋን ለማሻሻል እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
የተደረገው ድጋፍ በአጠቃላይ 27 ሚሊዮን ብር እንደኾነ ተገልጿል።
ነዋሪዎችም ወረዳው በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ጉዳት የደረሰበት በመኾኑ የተደረገው ድጋፍ አካባቢውን መልሶ ለማቋቋም እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
በቀጣይም የልማት ሥራዎች በስፋት እንዲከናዎኑ እና የአካባቢው ማኅበረሰብ ተጠቃሚ እንዲኾን በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን አስተዋጾ እንደሚያደርጉ አንስተዋል።
ዘጋቢ፦ ደረጀ ደርበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየባሕር ዳር ልዩ ውበት ድንቅ መልኮች!
Next articleያለ ፍትሕ ያጣችውን በፍትሕ ታስመልሳለች