ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የምሥራቅ አፍሪካን የቀጣና ትስስር እውን እያደረገ ነው።

4
ታዋቂው ዓለም አቀፍ የዜና ተቋም ሲኤንኤን (CNN) በቲክቶክ ገጹ ባሠራጨው ልዩ የቪዲዮ ዘገባ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ግዙፍነት እና ለምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ያለውን የላቀ ፋይዳ በስፋት አስተጋብቷል።
ከግድቡ ጠርዝ ላይ በመቆም ዘገባውን በቪዲዮ ያቀረበችው የሲኤንኤን ጋዜጠኛዋ ቪክቶሪያ ሩባዲሪ “እዚህ የግድቡ ጫፍ ላይ ስትቆም የዚህን ፕሮጀክት እውነተኛ ታላቅነት ትረዳለህ” ስትል አንጸባርቃለች። ግድቡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ቤት በብርሃን ከመሙላት ባለፈ ለጎረቤት ሀገራትም የኤሌክትሪክ ኃይል እያቀረበ ይገኛል” በማለት የፕሮጀክቱን ስፋት ገልጻለች።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዋና ሥራ አሥኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ ለሲኤንኤን በሰጡት ማብራሪያ ግድቡ በዓባይ ወንዝ ላይ የተገነባ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ መኾኑን ጠቅሰው በያዘው የውኃ መጠን በዓለም ላይ ካሉ ግዙፍ ግድቦች አንዱ መኾኑን አስገንዝበዋል።
ሲኤንኤን ጨምሮም ከ14 ዓመታት በላይ የፈጀው እና ባለፈው ዓመት መስከረም ወር ላይ በይፋ የተመረቀው ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት የኢትዮጵያውያን የምህንድስና ጥበብ የታየበት መኾኑን አስፍሯል። ግድቡ 145 ሜትር ከፍታ እና 1 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው መኾኑን ያስታወሰው ዘገባው “በእውነትም አስደናቂ እይታ ያለው ድንቅ አሻራ” ነው ሲል ገልጾታል።
ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ የኃይል ሽያጭ እና የቀጣናዊ ትስስሩን አስመልክቶ ለሲኤንኤን እንደተናገሩት በአሁኑ ወቅት ለኬንያ 200 ሜጋ ዋት ኃይል እየቀረበ መኾኑን ተናግረዋል። የኬንያ ማስተላለፊያ መስመር ግን እስከ 2 ሺህ ሜጋ ዋት የመሸከም አቅም አለው ብለዋል።
ጅቡቲ እና ሱዳን በአሁኑ ወቅት ከኢትዮጵያ የኃይል አቅርቦት ሥርዓት ጋር ሙሉ በሙሉ ተገናኝተዋል ነው ያሉት።
ከታንዛኒያ ጋር የመጀመሪያ ደረጃ የኃይል መስመር ትስስር ሥራው በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን ነው የተናገሩት።
ደቡብ ሱዳን እና ሶማሊያን በቅርብ ዓመታት ውስጥ ከኃይል መስመሩ ጋር ለማገናኘት መታቀዱን ገልጸዋል። በሂደት መላው የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና በኤሌክትሪክ ይተሳሰራል ነው ያሉት።
ይህ ግዙፍ የቀጣናው ትስስር ኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ገቢ እንድታገኝ የሚያስችላት መኾኑን የፕሮጀክቱ ዋና ሥራ አሥኪያጅ ጨምረው ገልጸዋል። ሲኤንኤን የሠራው ይህ ዘገባ ግድቡ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይኾን ለአጠቃላይ አሕጉራዊ ትስስር ያለውን ሚና በጉልህ ያሳየ ኾኗል።
በአድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleመጣና በዓመቱ ኧረ እንደምን ሰነበቱ…!
Next articleአዳሪ ትምህርት ቤቶች ለትምህርት ጥራት ያላቸው ዋጋ ከፍ ያለ ነው።