በኮሪደር ልማት የጎላው የቅርስ እና የውበት ቅብብሎሽ በሐረር!

8
የሥልጣኔ መነሻ እና የጠበብ መፍለቂያ የኾነችው የምሥራቋ ፈርጥ ሐረር ከተማ የንግድ፣ የፖለቲካ እና የማኅበራዊ ትስስር ማዕከል ኾና በትውልድ ቅብብሎሽ ከ1 ሺህ ዓመታት በላይ የተሻገረች ዕድሜ ጠገብ ከተማ ናት።
ለሺህ ዓመታት የተገነባ ታሪክ፣ ቅርስ እና ባሕል ባለቤት የኾነችው ሐረር ታሪኳን፣ ባሕሏን እና ቅርሷን ጠብቃ ለቀጣዩ ትውልድ በሚመች መልኩ በማስተላለፍ በምሳሌነት የምትጠቀስ ከተማ ናት።
በአሁኑ ወቅት በሐረር ከተማ በስፋት እየተተገበረ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት መሠረተ ልማትን ማሻሻል ብቻ ሳይኾን የክልሉን ባሕላዊ እና ታሪካዊ ዕሴቶች ከአዲሱ የከተማ ውበት ጋር አስተሳስሮ የመያዝ ትልቅ ራዕይ ያለው ተግባር ነው።
በዓለም አቀፉ የጀጎል ቅርስ በተሠራው የኮሪደር ልማት ሥራም የትላንትን ከዛሬ ጋር ጥንታዊነትንም ከዘመናዊነት ጋር አዋሕዶ የቅርስ መገኛ ለኾኑ አካባቢዎች ተምሳሌት በሚኾን ደረጃ አስደናቂ ሥራ ተከናውኗል።
በተከናወነው የኮሪደር ልማት ሥራም በእያንዳንዱ የሐረሪ ጥንታዊ ቤቶች በሚገኙ የታሪክ አሻራዎች እና የባሕል መገለጫዎች እንዲደምቅ እና ለነዋሪዎች ምቹ ለጎብኝዎች ተመራጭ የጉብኝት ሥፍራ እንዲኾን ማድረግ ተችሏል።
የኮሪደር ልማቱ የሐረር ታሪክ እና ቀደምት ሥልጣኔዋን በሚመጥን ደረጃ ፈጠራ፣ ፍጥነት እና ጥራት በተግባር የተረጋገጠበት ነው።
ወጣቱ ትውልድ ስለ ክልሉ ታሪክ እና ባሕል በመጽሐፍት ከመገንዘብ ባሻገር በጀጎል ዓለም አቀፍ ቅርስ የተሠሩ የኮሪደር ልማት ሥራዎችን እያየ እና እየዳሰሰ እንዲያድግ፣ ስለታሪኩ፣ ስለ ቅርሱ ያለው ፍቅር እና አክብሮት እንዲጎለብት የሚያደርግ ነው።
የጀጎል ዓለም አቀፍ ቅርስ እና በከተማው እውን የኾኑ የኮሪደር ልማት ሥራዎች ለጎብኝዎች እና ለነዋሪዎች አዳዲስ የጉብኝት እና የመዝናኛ አማራጮችን መፍጠር አስችሏል።
ይህም ከቱሪዝም ዘርፍ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ እና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ የቻለ ነው።
ከዚህ በተጨማሪ ቅርሶች ከጉዳት እንዲጠበቁ እና ተገቢውን እንክብካቤ እንዲያገኙ በማስቻል ረገድ አዳዲስ አሠራር አብሮ በመዘርጋት ታሪካዊ ሀብቶች ለክፍለ ዘመናት እንዲቆዩ በማድረግ ለመጪው ትውልድ ትልቅ ሀገራዊ ውርስ ኾኖ እንዲሸጋገር ያደርጋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleአፈሙዙን ዝጉ እና የሰላም ቄጤማን ለአዲስ ዓመት አምጡልን – የእናቶች ተማጽኖ
Next articleመጣና በዓመቱ ኧረ እንደምን ሰነበቱ…!