
ዓመት አልፎ ዓመት ሲተካ፤ ክረምቱ አልፎ አዲስ ዓመት ሲመጣ የሰው ልጆች በአዲስ መንፈስ፤ በአዲስ ተስፋ እና በአዲስ ሕልም ይቀበሉታል።
የኢኮኖሚ አቅማቸውን ለማሳደግ፤ ከፈጣሪ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር፤ ስብዕናቸውን ለመገንባት እና ሌሎች ዕቅዶችን ለመፈጸም ራሳቸውን ያዘጋጃሉ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን “ሀገር ሰላም ከኾነ” ተብሎ ማቀደም ተጀምሯል። በኢትዮጵያ ለዓመታት የቀጠለው የጸጥታ ችግር ማኅበረሰቡ ሰላምን እንዲጠማ አድርጎታል። ምድር አደይ አበባን ስትጎናጸፍ፤ የክረምቱ ጥቁር ዳመና ተገፎ የጠራ ሰማይ ሲገለጥ፤ ወንዞች ጎድለው ዘመድ አዝማድ በናፍቆት ሲገናኝ፤ በርካታ እናቶች ግን በግጭት እና ጦርነት ምክንያት ኦና ቤት ታቅፈው አውደ ዓመቱን ያሳልፋሉ።
ከአፈሙዝ የወጣ እሳት የልጇን ሕይወት የቀጠፈባት ቡና፤ ቄጤማ፤ በግ ገዝቶ “እንኳን አደረሰሽ እናቴ” ብሎ የሚያደምቃት ልጇን ሞት የነጠቀባት እናት ግን ቀጤማውም ጠፍቶ፤ ቡና እና ጭሱ ቀርቶ፤ በበጉ ፈንታ ልጇ ተሰውቶባት “እህህ” እያለች በእንባ እርሳ አውደ ዓመቱን ታሳልፋለች።
የሥልጣን ናፋቂዎች ሜዳ ላይ የልጇን ሕይወት ያስቀሩት ዘጠኝ ወር ተሸክማ አምጣ የወለደች እናት ከቶ አውደ ዓመቱን እንዴት ታሳልፈው ይኾን? ያዘጋጀችውን ምግብ እና መጠጥ ማን ይቀምስላት ይኾን? የሚለው የብዙዎች የሕሊና ጠባሳ ነው።
የግጭት አዙሪት የጎዳቸው እናቶች “አፈሙዙን ዝጉ እና ለአዲስ ዓመት የሰላም ቀጤማ አምጡልኝ” በማለት ሰላምን ይለምናሉ።
የትኛውም ጥያቄ በጦርነት ምላሽ አግኝቶ አያውቅም ይልቁንስ እናት ልጇን እንድታጣ፤ ሕጻናት ወላጅ በማጣት ጎዳና እንዲወድቁ፤ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት እንዲደርስ፤ ድህነት እንዲስፋፋ ያደርጋል እንጅ።
በአዲሱ ዓመት ግጭትን በውይይት በመፍታት አፈሙዝን በማጠፍ ለእናቶች የሰላም ቀጤማን ማቅረብ ያስፈልጋል።
የአማራ ክልል የሰላም እናቶች አባል ወይዘሮ አልጋነሽ አስፋው የሰላም እጦት በእናቶች፤ ሕጻናት እና አረጋዊያን ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ መኾኑን ተናግረዋል። ግጭቱ ሴቶች ለጥቃት እንዲጋለጡ እናቶች የሕክምና አገልግሎት እንዳያገኙ አድርጓል ብለዋል።
እናቶች የሀዘን ካባ ለብሰው፤ መቀነታቸውን ፈትተው ተንበርክከው እየለመኑ ነውና ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን በመቀበል ለእናቶች ተስፋ እንዲሰጡ አሳስበዋል።
እንደ ሰላም እናትነታቸው ከሃይማኖት አባቶች ጋር በመኾን ከ180 በላይ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭ እንዲቀበሉ ማድረጋቸውን ገልጸዋል። በቀጣይ በትኩረት እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
የሰላም በር መቼም አልተዘጋም ያሉት ወይዘሮ አልጋነሽ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን እንዲቀበሉ እና ሰላም እንዲሰፍን መልዕክት አሥተላልፈዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
