‎ዛሬ አንድ ኾነን ከተራመድን የማንሻገረው ወንዝ የለም።

3

‎ዛሬ አንድ ኾነን ከተራመድን የማንሻገረው ወንዝ የለም።

‎የሰላም ሚኒስቴር ከአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።

‎በመድረኩ የተገኙት የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ.ር) በክልሉ እና በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም፣ ወንድማማችነት እና አብሮነትን በጽኑ መሠረት ላይ ለመጣል በሚደረገው ጥረት ላይ በጋራ መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

‎በአማራ ክልል ባለፉት ጊዜያት በርካታ ፈተናዎች ተፈጥረው መቆየታቸውን ያነሱት ቢሮ ኀላፊው የሕዝቡ ጽናት እና አስተዋይነት የጥፋት ኀይሎችን አጀንዳ አክሽፏል ብለዋል።

‎”ዛሬ አንድ ኾነን ከተራመድን የማንሻገረው ወንዝ የለም” ያሉት ኀላፊው እናቶች፣ ወጣቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች አካባቢን ወደ ሰላም ለማምጣት እና ክልሉን ወደ ተሻለ መረጋጋት ለማሸጋገር በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል።

‎የሰላም ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ኀላፊ እና የሚኒስቴሩ ተወካይ መብራት ካሳ በክልሉ አሁን ያለው የሰላም እና መረጋጋት ሁኔታ ተስፋ ሰጭ መኾኑን ገልጸዋል።

‎በክልሉ የተገኘውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ሚኒስቴሩ የአቅም ግንባታ እና ሌሎችንም ድጋፎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል። ግጭቶችን በውይይት መፍታት እንደሚገባም አንስተዋል።

‎ሰላም የመንግሥት እና የጸጥታ አካላት ብቻ ሳይኾን የሁላችንም የጋራ ኀላፊነት ነው ያሉት በቢሮ ኀላፊ ደረጃ የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ኮሚሽነር ደጀኔ ልመንህ ናቸው።

‎በተለይም በማኅበራዊ ሚዲያ የሚተላለፉ አፍራሽ መልዕክቶችን በመግታት እና የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን በማጠናከር ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ በጋራ መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል።

‎በመድረኩ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኅላፊዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ሴቶች፣ ወጣቶች እና የሚመለከታቸው አካላት እየተሳተፉ ነው።

‎#አሚኮ#አማራክልል #ሰላም ኢትዮጵያ 🇪🇹

‎#ባሕር_ዳር #መስከረም_09_2019_ዓ_ም

‎በሥራውድንቅ ደሳለው

‎የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article‎በሰሜን ሸዋ ዞን የግሪሳ ወፍ ሰብል እንዳይጎዳ በአውሮፕላን የታገዘ የኬሚካል ርጭት እየተከናወነ ነው።