
በዞኑ ስምንት ወረዳዎች የግሪሳ ወፍ መከሰቱን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታውቋል።
በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ ታደሰ ማሙሻ ለአሚኮ እንደተናገሩት ክስተቱ ባጋጠማቸው አካባቢዎች የመከላከል ሥራ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።
የግሪሳ ወፍ የተከሰተባቸው አካባቢዎች፦ ቀወት፣ አንፆኪያ ገምዛ፣ ኤፍራታና ግድም፣ በረኸት፣ አንኮበር፣ ጣርማበር፣ ምንጃር ሸንኮራ ወረዳዎች እና ሸዋሮቢት ከተማ አሥተዳደር ናቸው።
ይህንን ተከትሎ የመከላከል ሥራ እየተከናወነ ሲኾን በአውሮፕላን የታገዘ የኬሚካል ርጭት በመካሄድ ላይ ነው ብለዋል ኀላፊው።
እስከአሁን በአንፆኪያ ገምዛ ወረዳ ሁለት የግሪሳ ወፍ ማደሪያ ጣቢያዎች ላይ ርጭት ተደርጎበታልም ነው ያሉት።
በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ የተከሰተውን ግሪሳ ለመከላከል ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር ርጭት ለመጀመር ዝግጅት ስለመደረጉም አብራርተዋል።
የግብርና ተቋማት መሪዎች እና ባለሙያዎች አስፈላጊውን ስምሪት ወስደው ግሪሳውን በመከላከል ላይ ናቸው ብለዋል።
ክስተቱ ባለባቸው ሁሉም ወረዳዎች የኬሚካል ርጭት ለማካሄድ የአቅጣጫ ጠቋሚ ሥራዎች ተሠርተው ስለመጠናቀቃቸውም አስገንዝበዋል።
ክስተቱ ባጋጠመባቸው አካባቢዎች ርጭቱ እስኪደርስ ሁሉም አርሶ አደሮች ወፉ አርፎ ሠብል ላይ ጉዳት እንዳያደርስ በባሕላዊ መንገድ መከላከል እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል።
#አሚኮ #የግሪሳወፍ_መከላከል #አማራክልል
#ኢትዮጵያ 🇪🇹
#ባሕር_ዳር #መስከረም_09_2019_ዓ_ም
ዘጋቢ፦ ኤልያስ ፈጠነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
