
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በ2018 በጀት ዓመት የፍርድ ቤቶችን የዕቅድ አፈጻጸም እና በ2019 በጀት ዓመት ተግባራት ዙሪያ ከሚመለከታቸው የዘርፉ መሪዎች ጋር እየመከረ ነው።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው በበጀት ዓመቱ በፍርድ ቤቶች ተስፋ ሰጭ ሥራዎች ተሠርተዋል ብለዋል።
በዳኝነት እና በፍትሕ ሥርዓቱ የተለያዩ የማሻሻያ ፕሮግራሞች ሲደረጉ መቆየቱንም ገልጸዋል። የለውጥ ሥራዎች፣ የዲጂታላይዜሽን፣ የሕግ ማዕቀፍ ማሻሻያ፣ የተቋም ግንባታ እና የሰው ሃብት ልማት ሥራዎችን ለአብነት አንስተዋል።
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱም በእነዚህ የማሻሻያ መርሐ ግብሮች መሠረታዊ ለውጦችን ማምጣት መቻሉን ነው የተናገሩት።
በመደበኛው የፍትሕ ሥርዓት እና በአማራጭ የዳኝነት አገልግሎት ሥርዓቶችም ውጤታማ ተግባራትን አከናውኗል ነው ያሉት።
በአፈጻጸም ግምገማው የፍርድ ቤቶች አፈጻጸም ከዚህ በፊት ከነበሩት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ መሻሻል ያታየበት ስለመኾኑም አብራርተዋል።
በውሳኔ ጥራት፣ በመዛግብት ብዛት፣ በቅልጥፍና እና በሌሎችም መለኪያዎች በበጀት ዓመቱ የላቀ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።
የፍርድ ቤቶችን አፈጻጸም ከመዋቅሩ በተጨማሪ በክልል ደረጃም የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሴቶች፣ የወጣቶች ተወካዮች በተገኘበት በዘርፉ ውይይቶች መደረጋቸውንም አንስተዋል።
የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን የለውጥ ሥራዎች በርካታ የክልል እና የፌዴራል የመንግሥት መሪዎች፣ የግል ድርጅቶች፣ የሲቪል ማኅበራት፣ የሃይማኖት ተቋማት ጎብኝተው ምስክርነት የሰጡበት ስለመኾኑም አብራርተዋል።
ከቀናት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ተገኝተው የተጀመሩ የዲጂታል እና የለውጥ ሥራዎችን በመጎብኘት ገንቢ አስተያየት መሥጠታቸውንም አንስተዋል።
የተጀመሩት የለውጥ ሥራዎች፣ የዲጂታል ችሎት እና ኢ ፋይሊንግ አሠራሮች ተስፋ ሰጭ መኾናቸውን እና ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተነስተዋል ነው ያሉት።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝትም ለቀጣይ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሥራዎች ትልቅ ኀላፊነትን የሚሰጥ፣ ትልቅ ዕድል ይዞ የሚመጣ፣ ተጨማሪ የለውጥ ሥራዎችም እንዲከናወኑ ስንቅ የሚኾን ነው ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
