
በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ጃዊ ወረዳ የሚሠበሠበው የቅባት ሰብል የሀገራዊ ኤክስፖርት እና የኢንዱስትሪ ፍላጎትን ለመደገፍ የታቀደውን የምርት ግብ ለማሳካት ወሳኝ ድርሻ ያለው ነው።
በአካባቢው የተስተካከለ ዝናብ መኖሩ በጊዜ የቀረቡ የግብርና ግብዓቶች የአፈር ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር እንዲሁም የባለሙያዎች ድጋፍ ተጣጥመው የወረዳውን የሰብል ቁመና ከባለፈው ዓመት በእጅጉ የተሻለ አድርገውታል።
በወረዳው ነዋሪ የኾኑት አርሶ አደር አታላይ መለሰ እና አርሶ አደር ይታየው አሳዬ እንደገለጹት በይዞታቸው ባለው መሬት ላይ ሰሊጥ፣ አኩሪ አተር እና ለውዝን ጨምሮ የተለያዩ የቅባት ሰብሎችን አልምተዋል።
አሁን ላይ ሰብላቸው በተባይ እና በአረም እንዳይጎዳ አስፈላጊውን እንክብካቤ እያደረጉ እንደሚገኙ እና ከፍተኛ ምርት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።
የጃዊ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አበራ ባዘዘው በበኩላቸው በወረዳው በበጀት ዓመቱ ከ131 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት ታቅዶ 99 በመቶውን ማልማት መቻሉን ገልጸዋል።
ከዚህ ውስጥ 77 ሺህ ሄክታሩ በቅባት እና ጥራጥሬ ሰብሎች የተሸፈነ ሲኾን ከ2 ሚሊዮን 700 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል።
በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት እና ጥበቃ ዳይሬክተር ማንደፍሮ አስላከ (ዶ.ር) እንደተናገሩት በክልሉ በ2018/2019 የመኸር እርሻ ለማልማት ከተታቀደው 5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር ውስጥ እስካሁን 5 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታሩ በዘር ተሸፍኗል። ከዚህ ውስጥ ከ557 ሺህ ሄክታር በላይ የሚኾነው በቅባት ሰብሎች የተሸፈነ ሲኾን 5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት እየተሠራ ይገኛል ነው ያሉት።
ምርቱ ለሀገር ውስጥ ፍጆታ እና ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት ከመኾን ባለፈ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ለሀገር ኢኮኖሚ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ተጠቅሷል።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ
