በባሕር ዳር ከተማ ባለፈው በጀት ዓመት ብቻ 41 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች ለልማት ገብተዋል።

8

 

የኢንዱስትሪ መሥፋፋት ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ድርሻው ከፍተኛ ነው። በተለይም በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በሀገር ውስጥ ምርት ዕድገት፣ በውጭ ምንዛሬ ግኝት እና በሌሎችም ዘርፎች ያለው አስተዋጽኦ ከፍ ያለ ነው።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ከለውጡ መንግሥት በኃላ በኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ዘርፍ በርካታ ለውጦችን ማስመዝገቡን የከተማዋ የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ አስታውቋል።

በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ማዕረግ የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኅላፊ ብርሃን ንጉሴ እንዳሉት ከተማዋ ከለውጡ መንግሥት በኋላ በዘርፉ በርካታ ውጤቶችን አስመዝግባለች።

በ2018 በጀት ዓመት በከተማዋ ውስጥ ባለሀብቶችን በኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመሳብ በተደረገው ጥረት 383 ባለሀብቶችን መሳብ መቻሉን ነው የገለጹት።

እነዚህ ባለሀብቶች 41ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ ሲኾን በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ ሲገቡ 47 ሺህ 655 ለሚኾኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ይችላሉ ብለዋል።

በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍም 23 ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ የገቡ ሲኾን በአገልግሎት ዘርፍም ወደ 32 የሚጠጉ ተቋማትን ሥራ ማስጀመር ተችሏል ነው ያሉት። ከ50 በላይ ድርጅቶች በችግሮች ውስጥ አልፈው ወደ ሥራ እንዲገቡም ተደርጓል። በዚህም 71 ነጥብ 3 ሄክታር መሬት ለሥራ የማስተላለፍ እና ከሦሥተኛ ወገን ነጻ የማድረግ ተግባራት ተሠርተዋል ብለዋል።

በተለይም ወደ ሥራ ያልገቡ ኢንዱስትሪዎችን ክትትል በማድረግም 81 ኢንዱስትሪዎች የቃል እና 58 ለሚኾኑ ደግሞ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ መሠጠቱን ገልጸዋል። ለአምራች ኢንዱስትሪዎች የብድር እና የተለያዩ ድጋፎች እየተደረገ መኾኑንም ነው የገለጹት።

ኢንዱስትሪዎችን ከደረጃ ደረጃ በማሽጋገር የማምረት አቅማቸውን የማሳደግ ተግባራት ማከናወን መቻሉንም አንስተዋል። ለኢንዱስትረዎች በተደረገው ድጋፍም የማምረት አቅማቸው ወደ 65 ነጥብ 10 በመቶ በአማካኝ ከፍ እንዲል ተደርጓል ብለዋል።

በከተማዋ 145 ስትራቴጂክ የገቢ ምርቶችን የሚተኩ አምራች ኢንዱስትሪዎች ይገኛሉ፤ እነዚህም 122 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማዳን መቻላቸውን አውስተዋል።

ከፌዴራል የኢንዱስትሪ መንደር ውጭ በአራቱ ክፍለ ከተሞች በግል ባለሀብቶች እየለሙ የሚገኙ 4 የኢንዱስትሪ መንደሮች መኖራቸውን ያነሱት መምሪያ ኅላፊዋ በቀጣይ ከ400 ሄክታር መሬት በላይ በኢንዱስትሪ መንደር ለማልማት ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

ከተማዋን ይበልጥ የኢንዱስትሪ እና የኢንቨስትመንት ማዕከል ለማድረግ አምራች ኢንዱስትሪዎችን የመደገፍ፣ የማነቃቃት እና የማምረት አቅማቸውን የማሳደግ ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተመላክቷል።

#AMECO #BahirDar #Investment🇪🇹

#ባሕር_ዳር #ነሐሴ_03_2018_ዓ_ም

በሥራውድንቅ ደሳለው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleሀገራዊ ምክክሩ የሁሉንም ዜጎች ንቁ ተሳትፎ የሚጠይቅ የጋራ አደራ ነው።
Next article🌳 አረንጓዴው ሀብታችን – ከተራቆተ መሬት እስከ ቢሊዮን ዶላር ገቢ! 🇪🇹 ☕🥑