ሀገራዊ ምክክሩ የሁሉንም ዜጎች ንቁ ተሳትፎ የሚጠይቅ የጋራ አደራ ነው።

8

 

ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ውስጥ ስታካሂደው የቆየችው አሁን ላይ ወደ ወሳኙና የመጨረሻው ምዕራፍ የተሸጋገረው የሀገራዊ ምክክር ሂደት የሀገሪቱን ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መልክ ለመወሰን ታላቅ ታሪካዊ በር ከፋች ኾኗል።

ከሐምሌ 08/ 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የሀገር ችግር ሊፈታ እየተንደረደረ ይገኛል። ለዚህም ከሁሉም የሀገሪቱ ማዕዘናት የተውጣጡ የሕዝብ ወኪሎች የሀገር አደራ ተቀብለውና ሀገራዊ እሳቤን ተላብሰው የአንዱን ችግር ሌላው እየተሰማው እየመከሩ ይገኛሉ። ይህ ሀገራዊ ጉባኤ የዜጎችን የረጅም ጊዜ ጥያቄዎች እና የጋራ መግባባት ፍላጎቶችን የሚፈትሽ ትልቅ ምዕራፍም ነው።

የሀገራዊ ምክክሩን ሂደት ከሦሥት መሠረታዊ ዕይታዎች የሚያዩት ምሁራን ከሰላም፣ ከዴሞክራሲያዊ ተቋማት ግንባታ እና ከማኅበራዊ ትስስር አንጻር ሲታይ ምክክሩን እንደትልቅ መዞሪያ ያዩታል።

የዲፕሎማሲ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁሩ እንዳለ ንጉሴ እንደሚሉት ሀገራዊ ምክክሩ ከማንኛውም የኀይል እርምጃ በላይ ትልቅ ጉልበት እና ፋይዳ አለው። ኢትዮጵያ ውስጥ ለበርካታ አሥርት ዓመታት የቆዩ አለመግባባቶች መፍትሔ ያጡት ግጭትን በግጭት ለመፍታት በመሞከር እንጂ በሰከነ ውይይት አይደለም ባይ ናቸው።

የምክክር ሂደቱ የኀይል አጠቃቀምን ባሕል በማስወገድ ልዩነቶችን በሠለጠነ የንግግር ማዕቀፍ ውስጥ የማስተናገድ አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ ያበስራል። የጠረጴዛ ዙሪያ ንግግር ማንም አሸናፊ እና ተሸናፊ ሳይኖር የጋራ ድልን የሚያስገኝ ብቸኛ መሣሪያ መኾኑንም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያውያን ያለፉትን ታሪካዊ እና ፖለቲካዊ ቁርሾዎች የሚፈቱበት አጋጣሚ ላይ ይገኛሉም ይላሉ።

በቅድመ ዝግጅት ውይይቶች የተከናወኑት የአጀንዳ ማሠባሠብ እና የተሳታፊዎች ልየታ ሥራዎች ሕዝቡ የሚፈልገውን እውነት በግልጽ እንዲያወጣ ከማድረግ በላይ ምክክሩ በውጤት እንዲታጀብ ያስችለዋል ባይ ናቸው።

እንደ ሀገር ግንባታ፣ የመንግሥት አደረጃጀት እና የሕግ የበላይነት የመሳሰሉት ዐበይት አጀንዳዎች መመረጣቸው ችግሮቹን ከመሠረታቸው ለማከም የሚያስችል ትክክለኛ የትኩረት አቅጣጫ እንደኾነም ጠቁመዋል።

ሀገራዊ ምክክሩ የይስሙላ የውይይት መድረክ ሳይኾን የሁሉንም ዜጎች ሁለንተናዊ ተሳትፎ የሚጠይቅ የጋራ አደራ ነው ይላሉ።

የጉባኤው ስኬት የሚመሠረተውም ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ተወካዮች በሚያሳዩት የዴሞክራሲ ብስለት እና የሀገር ፍቅር ላይ እንደኾነም አስረድተዋል።

ሂደቱ ሀገሪቱን አሸናፊ ከማድረግ በተጨማሪ የኢትዮጵያን ብዝኀነት እና ሰላም ያከበረ፣ የሁሉም ባለቤት የኾነች ሀገር ለመገንባት የሚያስችል ጠንካራ መሠረት ይጥላል ተብሎ ይጠበቃልም ብለዋል።

ከሐምሌ 08/2018 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ ያለው ይህ ታላቅ ሀገራዊ ጉባኤ ኢትዮጵያ ከነበረችበት የፖለቲካ ውጥረት እና ማኅበራዊ ቁርሾዎች ወጥታ ወደ ሁለንተናዊ ሰላም፣ እኩልነት እና ልማት የምትሸጋገርበትን አዲስ ምዕራፍ የሚከፍትም ነው ብለውታል።

#አሚኮ #ሀገራዊ_ምክክር🇪🇹

#ባሕር_ዳር #ነሐሴ_03_2018_ዓ_ም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleከሀገር ሉዓላዊነት እስከ ዓለም አቀፍ የሰላም አምባሳደርነት !
Next articleበባሕር ዳር ከተማ ባለፈው በጀት ዓመት ብቻ 41 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች ለልማት ገብተዋል።