
በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተካሄደ ባለው የምክክር ሂደት ውስጥ የአካል ጉዳተኞች መካተት የሂደቱን አሳታፊነት እና ሙሉነት እንደሚያረጋግጥ የደብረ ታቦር አካል ጉዳተኞች ማኅበር አስታውቋል።
ማኅበሩ ተወካዮቹን ወደ ኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በመላክ ንቁ ውይይት እያደረገ እንደሚገኝ የማኅበሩ ሠብሣቢ ብሩ ቸኮለ ተናግረዋል።
ሂደቱ በፖለቲካው ዘርፍ በአመራርነት ሚና፣ በኢኮኖሚው የባለቤትነት እና የተጠቃሚነት ዕድልን ከመፍጠር እንዲሁም ማኅበራዊ ፍትሕን ከማረጋገጥ አኳያ የጎላ ለውጥ ያመጣል የሚል ከፍተኛ ተስፋ መጣሉን ጠቁመዋል።
በደብረ ታቦር አካል ጉዳተኞች ማኅበር የዜጎች በጎ ፈቃድ አገልግሎት አካቶ ትግበራ ባለሙያ ቃልኪዳን ፈረደ የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎ በቁጥር ብቻ የሚወሰን መኾን የለበትም ብለዋል።
አቅምን በማሳደግ በሁሉም እንቅስቃሴዎች ውስጥ በእኩል ደረጃ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ማድረግ የላቀ ውጤት እንደሚያስገኝም አስገንዝበዋል።
የምክክር ኮሚሽኑ ሂደቱን በውጤታማነት በመምራት ሀገሪቱን ከገባችበት ቀውስ ሊያወጣ እንደሚችል የጠቆመው ማኅበሩ በታችኛው የኅብረተሰብ ክፍል የሚገኙ እና በተለያዩ ግጭቶች አካላቸውን ያጡ ዜጎች ተጠቃሚ የሚኾኑበትን አሠራር መንግሥት እንዲዘረጋም ጥሪ አቅርቧል።
በተጨማሪም ውይይቱ ያለፉ ችግሮች ላይ ብቻ ትኩረት ከማድረግ ይልቅ የሀገሪቱን የወደፊት የጋራ ዕጣ ፈንታ በሚወስን መልኩ መመራት እንዳለበት ማኅበሩ መልዕክቱን አስተላልፏል።
ዘጋቢ፦ ተክለብርሃን ፈንታ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
