የዘመናት ቋጠሮዎችን በመፍታት አዲስ የፖለቲካ ባሕል የመገንባት ታሪካዊ ምዕራፍ።

9
ኢትዮጵያ ለዘመናት ተንከባለው የመጡ ውስብስብ የፖለቲካ ሽኩቻዎችን፣ የታሪክ ተቃርኖዎችን እና የማኅበራዊ አለመግባባት ቋጠሮዎችን በዘላቂነት ለመፍታት ያለመውን ታሪካዊ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ እያካሄደች ትገኛለች። ጉባኤው ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተወከሉ ተሳታፊዎችን በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ በማሠባሠብ በጋራ መግባባት ላይ የተመሠረተ ቅቡልነት ያለው ሀገረ-መንግሥት ለመገንባት የተጣለ ትልቅ ተስፋም ነው።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሂደቱን አካታች፣ አሳታፊ እና ተዓማኒ ለማድረግ የተከተለው “ከታች ወደ ላይ” የኾነ አሠራር የምክክሩ ዋና መሠረት ነው። በዚህ ምክክር በሁሉም ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ አሥተዳደሮች የተካሄዱ ሰፊ ሕዝባዊ ውይይቶች ዋናውን ምክክር አካታች አድርጎታል። በምክክሩም 1ሺህ 234 ወረዳዎች እንዲሳተፉ መደረጉ ምክክሩ ሕዝባዊ እንዲኾንም ያስቻለ ኾኗል።
ይህ ሂደት አርሶ አደሮችን፣ አርብቶ አደሮችን፣ ሴቶችን፣ ወጣቶችን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ የሲቪክ ተቋማትን፣ ምሁራንን እና የማኅበረሰብ መሪዎችን ያለልዩነት ያሳተፈ ሲኾን፤ ገለልተኝነትን እና ግልጽነትን ባስጠበቀ መልኩ ተሳታፊዎችን የመለየት ሥራ መከናወኑን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መሥፍን አርዓያ ይገልጻሉ።
የሀገራዊ ምክክሩ አጀንዳዎችም የዓለም አቀፍ ልምዶችን፣ የጥናት ግኝቶችን እና ሳይንሳዊ ሂደቶችን ተከተለው የተቀረጹ መኾናቸው የሕዝቡን እውነተኛ ቅሬታዎች፣ ስጋቶች፣ ፍላጎቶች እና መጻኢ ተስፋዎች እንዲያካትት አስችሎታል።
በዚህ መድረክ ላይ መንግሥትም ቢኾን እንደ አንድ ተሳታፊ የራሱን አጀንዳ የሚያቀርብበት እንጂ ሂደቱን ሙሉ በሙሉ የሚቆጣጠርበት ባለመኾኑ ኮሚሽኑ የሕዝብ ባለቤትነትን እና ባለአደራነትን ያረጋገጠበት ነው።
ሀገራዊ ምክክሩ የሀገሪቱን መፍረስ የሚመኙ የውስጥ እና የውጭ ተደራራቢ ጫናዎችን እንዲሁም ሀሰተኛ መረጃዎችን በማከሸፍ ምክክሩን እውን ማድረግ የቻለም ነው።
ጉባኤው እርስ በእርስ የመደማመጥ፣ የሌላውን ሕመም የመረዳት እና በየጊዜው የሚያመረቅዙ ታሪካዊ ትርክቶችን እና ቁስሎችን የማከም ትልቅ ኀላፊነት ተጥሎበታል።
ይህ መድረክ ልዩነቶችን የብዝኀነት ውበት በማድረግ፣ በመንግሥት እና በሕዝብ መካከል የተቃጣውን መተማመን በመመለስ እና ለቀጣዩ ትውልድ የተረጋጋች ሀገር ለማስረከብ የተጣለ ጽኑ መሠረት ነው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየውበት ልኳ ባሕር ዳር
Next articleምን ያህል ያስጠይቃል?