
በጎንደር ከተማ አሥተዳደር “ተስፋን እንትከል” በሚል መሪ መልዕክት በተካሄደው የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በ15 ቦታዎች ላይ ከ376 ሺህ በላይ ችግኞች ተተክለዋል።
የከተማ አሥተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ ከ4 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ችግኞች የሚተከሉ ሲኾን እነዚህም የደን ሽፋንን ከመጨመር ባሻገር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ይረዳሉ።
ባለፉት ዓመታት ከተተከሉት ችግኞች ውስጥ ከ80 በመቶ በላይ መጽደቃቸውን እና ወጣቶችም በንብ ማነብ ሥራ ተሰማርተው የሥራ ዕድል ማግኘታቸውን ጠቁመዋል።
ቀጣይም የተተከሉት ችግኞች እንደ መገጭ እና ጣና ሐይቅ ያሉ የውኃ አካላትን ከደለል ከመጠበቅ በተጨማሪ፣ ለወጣቶች ተጨማሪ የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ ከተማ አሥተዳደሩ አስፈላጊውን እንክብካቤ እና ትኩረት እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።
ዘጋቢ:- ደስታ ካሳ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
