የተሰበረው የካይሮ ሕልም እና አይበገሬው የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት

6

 

ግብጽ በኢትዮጵያ ላይ የምትከተለው የውጭ ፖሊሲ ኢትዮጵያን በማዳከም ላይ የተመሠረተ ነው። ኢትዮጵያን በወታደራዊ፣ በዲፕሎማሲያዊ እና በውስጥ ግጭት በማዳከም ዓባይን በብቸኝነት ተቆጣጥራ መጠቀም የሁልጊዜም ስትራቴጂካዊ መርሕ እና አቋሟ ነው።

የግብጽ ገዢዎች ከሙሐመድ አሊ ፓሻ እስከ ገማል አብደል ናስር፣ ከከዲቭ እስማኤል ፓሻ እስከ አብደል ፈታህ አል ሲሲ አሥተዳደራቸው በዚህ መርሕ ላይ የቆመ ነው።

ግብጽ በቀጣናው የበላይነቷን ለማስጠበቅ በመስፋፋት ፖሊሲ ሱዳንን ጨምሮ የቀንዱ ሀገራትን፣ ምጽዋን እና የቀይ ባሕርን በእጇ ማስገባት የዘመናት ህልሟ ነው። ይህንን ለማሳካት በርካታ ወረራዎች መፈጸሟን የታሪክ ጸሐፊው ተክለ ጻዲቅ መኩሪያ “አጼ ዩሐንስ እና የኢትዮጵያ አንድነት” በሚለው መጽሐፋቸው በስፋት አብራርተውታል።📚

በታሪክ ከአረብ ሀገራት እስከ ምዕራባውያን፣ ከመካከለኛው ምሥራቅ እስከ ሩቅ ምሥራቅ ሀገራት በዘለቀ የዲፕሎማሲ ጫና ተጽዕኖ ለማድረግ ጥራለች።🌐

ቀደም ባሉት ዘመናት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ ሳይቀር “ዓባይን የምትነኩ ከኾነ ጳጳስ አንልክላችሁም” የሚል የእጅ አዙር ሃይማኖታዊ ስትራቴጅ ለመጠቀምም ሞክራለች።

በ19ኛው ክፍለ ዘመን በኢትዮጵያ ላይ የቀጥታ ወታደራዊ ዘመቻዎችን አድርጋለች። ለአብነት በጉንደት እና ጉራ ጦርነቶችን በማካሄድ ኢትዮጵያን ለመውረር ብትሞክርም የኢትዮጵያ ሠራዊት የግብጽን ወራሪ ኃይል አሳፍሮ መልሶታል።

በወረራ ኢትዮጵያን ማሸነፍ ያልቻለችው ግብጽ ስልቷን ቀይራ ውስጣዊ አንድነትን ማዳከም የዓላማዋ ማስፈጸሚያ ስትራቴጅ አድርጋ ትጠቀማለች። በሚቺጋን ስቴት ዩኒቨርሲቲ የሰሜን ምሥራቅ አፍሪካ ጥናቶች ውስጥ “ግብጽ እና የዓባይ ፖለቲካ (ዳንኤል ኪዳኔ:1999)” በሚል ርዕስ የታተመው ጥናትም ይህንኑ ያረጋግጣል።

“ኢትዮጵያ ስትዳክም እና በውስጥ ስትከፋፈል ግብፅ እረፍት ታገኛለች። ነገር ግን ኢትዮጵያ ስትበለጽግ፣ በራሷ ስትተማመን እና ቀጣናው ውስጥ መሪ ሚና ስትጫወት ግብፅ ትጨነቃለች” በማለት ግብጽ በኢትዮጵያ ላይ ያላትን የውጭ ፖሊሲ በግልጽ ይተነትናል።📖

በተለያዩ ዘመናት ለአማጺ ቡድኖች በካይሮ ቢሮ ከመክፈት፣ በገንዘብ፣ በወታደራዊ በሥልጠና እና በዲፕሎማሲ እስከመደገፍ የሚደርስ የትርምስ እቅዶችን በመንደፍ በኢትዮጵያ ላይ ጥቅሟን የማስከበር ምኞቷን እውን ለማድረግ ሞክራለች፤ ግን አልተሳካላትም።

​⚠️ አሁንም የሻብያን፣ የሕወሃትን እና ሌሎችንም የሀገር ውስጥ ታጣቂዎች በማሰባሰብ “ጽምዶ” የሚል ጥምረት በመፍጠር እየደገፈች መኾኑን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገልጸዋል። ይህም ኢትዮጵያን ከጀርባ በመውጋት እና በውክልና ጦርነት ከውስጥ ረፍት በመንሳት ፍላጎቷን ለማሳካት ዛሬም እየጣረች ስለመኾኑ ማረጋገጫ ነው።

​❓ይህ የዛሬው የግብጽ ፍላጎት ምንጩ የኢትዮጵያውያንን ታሪካዊ ማንነት ከመካድ? ከመርሳት ወይስ ከከንቱ ምኞት?

ግብጽን በጉንደት እና ጉራ፣ ጣልያንን በአድዋ፣ የዚያድባሬን ጦር በኦጋዴን፣ ደርቡሽን በኩፊት ያሸነፈው የኢትዮጵያ ሕዝብ የውስጥ ልዩነቶችን ትቶ በሀገር ሉዓላዊነት በሚመጣ ኃይል እንደማይደራደር የሚያረጋግጡ አብነት የታሪክ ምስክሮች ናቸው።​🔥

ኢትዮጵያ ዛሬም ይህንን የብሔራዊ አርበኝነት የሚያስቀጥል ትውልድ ያላት ሀገር መኾኗን ጠላቶች መርሳት እንደሌለባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ያስገነዝባሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ማንም ጣልቃ እንዲገባ ዕድል መሥጠት የለብንም ብለዋል።

ውስጣዊ የአለመግባባት ፈተናዎችን “መቋቋምን”፣ ፈተናን ወደ ዕድል ቀይሮ “መጠቀምን”፣ አጀንዳ ፈጥሮ “መግራትን” መርሕ አድርገን መሥራት ይጠበቃል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ጠላቶች ስሌት ኢትዮጵያ ድልብ ሃብት፣ የማይገዛ ሕዝብ፣ ሊገዟት ሞክረው በተደጋጋሚ አሳፍራ የሰደደቻቸው ሀገር መኾኗን በ”መካድ” የሚመጡ ናቸው ብለዋል። የተቋማዊ ልምምዳችንን እና እምቢ ባይነታችንን በ”መርሳት” የሚመጡ መኾናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል።

በቀደመ ስልት እስረኛ በመኾን ዛሬም ያንን መንገድ በመከተል ኢትዮጵያን የማንበርከክ ከንቱ “ምኞት” ላይ የተመሠረተ ሌላው የጠላቶች ስልት ስለመኾኑም ጠቁመዋል።

ለዘመናት በቀጥታ ወረራ ሞክረው መሸነፋቸውን የካዱት ግብጾች እና መሰሎቿ ዛሬም በኢትዮጵያ ላይ ዳግም መነሳታቸው የመካድ፣ የመርሳት እና የከንቱ ምኞት ስሌት መኾኑን ያስታውሰናል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ “እንኳንስ ሕወሃት፣ ሻብያ፣ ግብጽ እና ሱዳን ቀርቶ ማንም ቢመጣ በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት በኩል ቅንጣት ታክል ስጋት የለም” በማለት የኢትዮጵያን ዝግጁነት አረጋግጠዋል።

#Ameco ​#የኢትዮጵያ 🇪🇹​#EthiopianSovereignty
#ባሕር_ዳር #ሐምሌ_19_2018 ዓ_ም

✍️በአሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleየአካባቢ ጥበቃ ዋና የመንግሥት ትኩረት ነው።
Next articleሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ ድምጹን እያሰማበት ያለ ታሪካዊ ዕድል!