
የጤና ሚኒስቴር የዘንድሮውን ሀገር አቀፍ የክረምት በጎ ፈቃድ የጤና አገልግሎት መርሐ ግብር አስጀምሯል።
በዘንድሮው የክረምት የበጎ ፈቃድ መርሐ ግብር ከሕክምና አገልግሎት ባሻገር ልዩ ልዩ ማኅበራዊ ተግባራት እንደሚከናወኑ ተገልጿል።
በመድረኩ እንደተገለጸውም ለ20 ሚሊዮን ዜጎች ነጻ የጤና ምርመራ፣ የምክር እና የሕክምና አገልግሎት ይሰጣል ተብሏል።
በበጎ ፈቃድ ሥራው የደም ልገሳ ተግባር ይከናወናል፤ የጤና ተቋማትን ጽዱ የማድረግ ዘመቻ እና የወባ መከላከል ሥራዎች እንደሚሠሩም ተብራርቷል።
አቅመ ደካማ ለኾኑ እና ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ዜጎች የቤት ግንባታ እና እድሳት እንደሚደረገም ተገልጿል። ለተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ይቀርባል፤ የችግኝ ተከላ ይከናወናል ነው የተባለው።
ባለፈው በጀት ዓመት የተበላሹ የሕክምና መሣሪያዎችን በመጠገን ከፍተኛ ወጭ ማዳን መቻሉም ተመላክቷል። ዘንድሮም የሕክምና መሣሪያዎች ጥገና ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተብራርቷል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ የክረምት የበጎፈቃድ አገልግሎት ሳይቋረጥ የሚሠራ ሥራ መኾኑን ጠቅሰዋል።
ጤና ሚኒስቴር ሙሉ የጤና አገልግሎት ከመስጠት ባለፈ ሁሉንም ማኅበረሰብ ተጠቃሚ ያደረገ የማኅበራዊ አገልግሎት ሥራ እየሠራ ይገኛል ነው ያሉት። በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) አነሳሽነት የተጀመረው ይህ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ባሕል የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ባለፈ ለበርካታ ዜጎች የሕይወት ዋስትና እየኾነ ይገኛል ብለዋል።
እስካሁን በተከናወነው የክረምት ሕክምና በጎ ፈቃድ አገልግሎት በርካታ ዜጎች የነጻ የጤና አገልግሎት ማግኘታቸውን አመላክተዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ሎሚ በዶ የክረምት ወራት በኢትዮጵያ የመረዳዳት እና የመደጋገፍ ወቅት መኾኑን ገልጸዋል። የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱን በጤና ሥርዓቱ ውስጥ አካቶ ማስኬድ ለሌሎች ሀገራት ጭምር ተምሳሌት የሚኾን ተግባር ነው ብለዋል።
ባለሙያዎችም ያሉትን ውስን ሀብቶች በአግባቡ በመጠቀም የተጀመረውን ልማት እንዲያጠናክሩ እና ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ ባለፉት ዓመታት በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ ከፍተኛ እና የላቀ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ክልሎች ዕውቅና እና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
#አሚኮ #ሀገር_አቀፍ_የክረምት_በጎ_ፈቃድ #የጤና_አገልግሎት_መርሐ_ግብር #ኢትዮጵያ
#አዲስ_አበባ፡ ሐምሌ 10/2018 ዓ.ም
ዘጋቢ፦ ሰለሞን አሰፌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
