
የአማራ ክልል የንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ የግብይት ሥርዓቱን ለማስተካከል፣ የገበያ ተደራሽነትን ለማስፋት እና የኑሮ ውድነትን ለማቃለል የሚያስችሉ ሥራዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው።
የቢሮው ምክትል ኀላፊ አትክልት አሳቤ በክልሉ የከተማ ልማት ክላስተር ውይይት ላይ በተገኙበት ወቅት እንዳስታወቁት በክልሉ የተገነቡ የሁለተኛ ደረጃ የገበያ ማዕከላት በሁሉም ቀናት በቂ ምርት እንዲኖራቸው እየተሠራ ነው።
ከ300 በላይ ነባር የእሑድ ገበያዎችም በቂ ምርት የሚቀርብባቸው እንዲኾኑ እየተሠራ እንደኾነ አስገንዝበዋል። የግብይት ሥርዓቱን የድንኳን ገበያዎችን በማስፋት በተደራሽነት የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት ትኩረት መሰጠቱንም ተናግረዋል።
በፍኖተ ሰላም፣ እንጅባራ፣ ሁመራ፣ ገንዳ ውኃ፣ ሰቆጣ እና ከሚሴ ከተሞች እየተገነቡ ያሉ ዘመናዊ የገበያ ማዕከላትን ግንባታም በክረምቱ የ90 ቀናት ዕቅድ ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነው ብለዋል። ግንባታቸው በሪጆኦ ፖሊታን ከተሞች በተሠራው የገበያ ማዕከላት ስታንዳርድ ልክ እየተከናወኑ ስለመኾኑም አብራርተዋል።
እነዚህም አምራች እና ሸማችን በቀጥታ በማገናኘት የኑሮ ውድነቱ ከማኅበረሰቡ አቅም በላይ እንዳይኾን እገዛቸው የጎላ ስለመኾኑም ነው የተናገሩት።
ሕገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎችን እና የኮንትሮባንድ ሥራዎችን ለመከላከል ከአዲሱ በጀት ዓምት መግቢያ ጀምሮ ጥብቅ የፍተሻ እና የቁጥጥር ሥራዎችን በመተግበር ላይ መኾናቸውንም አስታውቀዋል።
የክልሉ ፖሊስ፣ የፍትሕ እና የጸጥታ አካላትን ያካተተ ኮሚቴም ያለምንም ምክንያት ዋጋ በሚጨምሩ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ለመውሰድ በቅንጅት እየሠሩ ነው ብለዋል።
የግብርና ምርቶችን በቀጥታ ከሸማቹ ጋር በማገናኘት የደላላ ጣልቃ ገብነትን ለማስቀረት፣ ለአቅራቢዎች፣ ለላኪዎች እና ለፋብሪካዎች ምቹ የግብይት መንገዶችን በመፍጠር የግብይት ሰንሰለቱን ለማሳጠር ጥረት እየተደረገ ስለመኾኑም ነው ያብራሩት።
የግብርና እና የእንስሳት ሀብት ልማት ተቋማትም ምርትን በማሳደግ ገበያውን የማመጣጠን ኀላፊነት ወስደው መሥራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
ኢንዱስትሪዎችንም በስፋት እንዲያመርቱ መከታተል እና መቆጣጠር ይገባል፤ ሌሎች አልሚዎችም ወደ ሥራ እንዲገቡ ማበረታታት ለኑሮ ውድነት ምላሽ ለመስጠት መሠረት መኾናቸውን ተናግረዋል።
የኑሮ ውድነትን ከሚያባብሱ ዋና ዋና ምክንያቶች መካከል አንዱ የኾነውን የቤት ኪራይ ችግርን ለመፍታት በከተማ ልማት ክላስተር ደረጃ በሰፊው እየተገመገመ በቅንጅት እየተሠራበት ይገኛልም ነው ያሉት።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ያጋጠመውን የነዳጅ እጥረት ተከትሎ በክልሉ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት ልዩ የክትትል ክፍል ተቋቁሞ ለግብርና፣ ለኤክስፖርት፣ ለፋብሪካዎች እና ለሕዝብ ትራንስፖርት ቅድሚያ በመስጠት ስርጭቱ እንዲከናወን መደረጉንም አስታውሰዋል።
በነዳጅ ሕገ-ወጥ ዝውውር ላይ በተደረገ ቁጥጥርም ከ22 በላይ በሚኾኑ ባለሙያዎች ላይ ሕጋዊ እና አሥተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱን አስታውቀዋል። በሂደቱም ሕገወጥ ነዳጅ መያዙን ነው የተናገሩት።
በአሁኑ ወቅት የነዳጅ አቅርቦቱ ወደ መደበኛ ስርጭቱ ተመልሶ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የግብይት ሥርዓት ተግባራዊ እየተደረገ ስለመኾኑም አስገንዝበዋል።
#ባሕር_ዳር፡ ሐምሌ 10/2018 ዓ.ም
በስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
