የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በጋራ መሥራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ።

9
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ጋር በፍርድ ቤቶች አገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያ ላይ በትብብር ለመሥራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ነው የተፈራረሙት።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሰፋፊ የለውጥ ሥራዎችን እያከናወነ ነው ብለዋል።
የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የዳኞችን እና የአሥተዳደር ሠራተኞችን የአጭር እና የረጅም ትምህርት ሥልጠናዎችን በመሥጠት የተለያዩ ተግባራቶችን እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
ነጻ የሕግ ድጋፍ፤ የጥናትና ምርምር ሥራዎች እንዲሁም የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ በጋራ ለመሥራት ስምምነት መደረጉን ነው የተናገሩት።
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የዕውቀት አሥተዳደር፤ የምርምር ዳይሬክትሬት ፤ በሕግ እና በፍትሕ ጉዳዮች የልህቀት ማዕከል ኾኖ የሚሠራ የሕግ እና የፍትሕ ኢንስቲቲዩት በመኖሩ በትብብር ለመሥራት ትልቅ ዕድል የሚሰጥ ነው ብለዋል።
ዩኒቨርስቲው ማኅበራዊ ኀላፊነቱን እንዲወጣ ዕድል የሚሰጥ መኾኑንም ተናግረዋል።ስምምነቱ ወደ ተግባር ወርዶ ማኅበረሰቡ ጋር ለውጥ እንዲያመጣ እንሠራለን ነው ያሉት። ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲን ጨምሮ ከሌሎች ዩኒቨርስቲዎች ጋር በጥምረት እየሠራ ነው ብለዋል።
የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ሳይህ ካሳው (ዶ.ር) የዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤቱ አያሌ የሕግ ምሁራንን አሠልጥኖ አስመርቋል ብለዋል። ከስምምነቱ በፊት ከጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ጋር በጋራ ሥንሠራ ቆይተናል ያሉት ፕሬዝዳንቱ በቀጣይም ስምምነቱን ተግባር ላይ በማዋል ውጤታማ ተግባራትን ለማከናወን እንደሚሠራ ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲው ለአቅመ ደካሞች ነጻ የሕግ አገልግሎት ለማኅበረሰቡ በመሥጠት መልካም ተግባር እየፈጸመ ነው ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር ስምምነት በመፈጸም በምርምር፤ በመማር ማስተማር፤ በማኅበረሰብ ዓቀፍ አገልግሎት ዘርፍ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ስምምነቱ ግንኙነትን የሚያጠናክር፤ ይበልጥ ወደ ተግባር ለመግባት የሚያግዝ፤ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ ውጤታማ ሥራዎችን እንድንሠራ የሚያስችል ነው ብለዋል። ምቹ የሥራ ሁኔታን የሚፈጥር መኾኑንም ገልጸዋል።
በቀጣይ ውጤታማ ሥራዎችን በጋራ እንፈጽማለን ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየኮሌራ ወረርሽኝ ሥጋት ነውን?
Next articleአምራች እና ሻጭን በቀጥታ የሚያገናኙ የገበያ ማዕከላት ግንባታ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል።