
የአማራ ክልል መሬት ቢሮ፤ የአካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን እና የኅብረት ሥራ ኮምሽን የሥራ ኀላፊዎች እና ሠራተኞች
“ተስፋን እንትከል” በሚል መሪ መልዕክት በባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር በዘንዘልማ ቀበሌ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አካሂደዋል።
የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ኀላፊ ሲሳይ ዳምጤ መንግሥት ውጤታማ የአረንጓዴ አሻራ ልማት እያከናነ ነው ብለዋል። በ6ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ከ3ሺህ በላይ ችግኝ መተከሉንም ገልጸዋል።
ወይራ፤ ዝግባ እና ግራቢላ ችግኞች መተከላቸውንም አንሥተዋል። በቀጣይ የአረም ማስወገድ፤ የመኮትኮት እና የተተከሉ ችግኞች እንዲጸድቁ ለማድረግ ይሠራል ነው ያሉት። ዘመናዊ ግብርናን እውን ለማድረግም መሬትን መንከባከብ ያስፈልጋል ብለዋል። ከማኅበረሰቡ ጋር በመቀናጀት እንዲጸድቁ ይሠራል ነው ያሉት። የአማራ ክልል አካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ኀላፊ ተሾመ አግማስ ለቀጣዩ ትውልድ የለመለመች፤ በደን የተሸፈነች ሀገርን ለማውረስ የችግኝ ተከላን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።
ባለ ሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ከተለያዩ አካላት ጋር በመኾን 100 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል እየተሠራ ነው ብለዋል። የተተከሉ ችግኞች እንዲጸድቁ ለማድረግም ትኩረት መሠጠቱን አንስተዋል።
በችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ ላይ የተሳተፉት የአካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን የደን ባለሙያ መንግሥቱ አገኘሁ በችግኝ ተከላ አሻራቸውን በማስቀመጣቸው ደስተኛ መኾናቸውን ተናግረዋል።
ለችግኝ ተከላ የሚኾን ጉድጓድ ቀድሞ በማዘጋጀት፤ ሙያዊ አሠራርን በመከተል ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል። የችግኝ ተከላው የወይራ እና ዝግባ ሀገር በቀል ችግኞች እንዳይጠፉ የሚያግዝ መኾኑን አንስተዋል።
የአማራ ክልል ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ባለሙያ አበራሽ ጣውየ የኅብረት ሥራ ማኅበራት በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በመሳተፍ በየወቅቱ ችግኝ በመትከል የበኩላቸውን እየተወጡ እንደሚገኙም አብራርተዋል። የተተከሉ ችግኞች እንዲጸድቁ በቅንጅት እንደሚሠሩም ገልጸዋል።
#ባሕር_ዳር፡ሐምሌ 9/2018 ዓ.ም
ዘጋቢ:-ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
