የትናንቱ ዓድዋ እና የዛሬው ትውልድ ጉዞ – የኢትዮጵያ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ

8

ኢትዮጵያ በትናንት ታሪኳ የአፍሪካና የዓለም ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ተምሳሌት መሆኗ በታሪክ ድርሳናት ተሰንዶ ይገኛል። አባቶቻችን በዓድዋ ጦርነት የማይገሰስ ደማቅ ታሪክ ጽፈዋል፤ የውጭ ወራሪ የኾነውን የጣሊያንን ጦር ድል በማድረግ ሀገራቸውን ሳያስደፍሩ አቆይተዋል። ይህ ኩሩ ታሪክ ዛሬም ድረስ ለትውልዱ ትልቅ የሞራል ስንቅ ኾኖ ያገለግላል።

ይሁን እንጂ የኢትዮጵያን ማደግ እና መበልጸግ የማይፈልጉ ኅይሎች ዝም አላሉም። ሀገሪቱ በቀጠናው ተጽዕኖ ፈጣሪ እንዳትኾን ተግተው ሠርተዋል፤ የሕዳሴ ግድብን እውን እንዳይኾን በብዙ አቅጣጫ ዘምተዋል። ከዚህም አልፎ እርስ በርስ የማይስማማና ለጋራ ዓላማ የማይቆም ትውልድ ለመፍጠር ጥረዋል።

ሴራቸው ደካማ እና ዝቅ ያለች ኢትዮጵያን ፈጥረው የራሳቸውን የበላይነት ለማስጠበቅ ዓለማ ያደረገም ነው። የዛሬው ትውልድ ግን ይህንን የውጭ ኃይሎች ሴራ በሚገባ ጠንቅቆ በማወቅ በሕዳሴ ግድብ ላይ የተሸረበውን ተንኮልና ጫና በማፍረስ ግድቡን ለስኬት እንዳበቃ ሁሉ አንድነቷ የተጠበቀች ጠንካራ ሀገር ለመገንባት ምክክሩን ጀምሯል። ኢትዮጵያዊያን ከተባበሩ የማያልፉት ፈተናና የማያሳኩት ድል እንደሌለም ታሪክ ይመሰክራል።

የአሁኑ ትውልድም ከፋፋዮችን ወደ ጎን በመተው በምክክር ሰላሟ የሚፀና ሀገር ለቀጣዩ ትውልድ ለማስረከብ እየተጋ ነው። ኢትዮጵያዊያን ልዩነቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት በአንድ አዳራሽ ተሰባስበው እየመከሩ ነው። ይህ የሰላምና የአንድነት ጉዞ ኢትዮጵያ አዲስ የብልጽግና ታሪክ ለመጻፍ ጫፍ መድረሷን የሚያሳይም ነው።

የኢጋድ ዋና ጸሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ.ር) ዛሬ ለኢትዮጵያ በታሪኳ ረጅምና ኩሩ በኾነው ጉዞዋ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ታሪካዊ ቀን ነው በማለት ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል። ኢትዮጵያ የራሷን ቁስል የምታክምበትና ችግሮቿን የምትፈታበት ጥንታዊና ጥልቀት ያላቸው የሽምግልና ጥበብ እንዳላት ለዓለም የምታሳይበትን ምክክር እያደረገች ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ታሪክ ወደፊት የሚሰራው በመነጋገር እንደኾነ የገለጹት ዶክተር ወርቅነህ፣ ኢጋድ በዚህ የውይይትና የምክክር ጉዞ ላይ ከኢትዮጵያ ጎን እንደሚቆም አረጋግጠዋል። ውይይቱና ውጤቱ የአፍሪካ ቀንድን ወደ ብሩህ ተስፋ የሚመራ ታላቅ እርምጃ መኾኑን በጽኑ እንደሚያምኑበትም መስክረዋል።

#Ethiopia #NationalDialogue #ሀገራዊምክክር #ኢትዮጵያ #ሰላምናአንድነት
#ባሕር_ዳር፡ ሐምሌ 09/2018 ዓ.ም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ስማቸው አጥናፍ

Previous article🇪🇹 ኢትዮጵያ አዲስ ታሪክ በምክክር እየጻፈች ነው🕊️
Next articleዘመናዊ ግብርናን እውን ለማድረግ መሬትን መንከባከብ ያስፈልጋል።