
ታላቋ ኢትዮጵያ ሀገራዊ ችግሮቿን ትፈታ ዘንድ ሀገራዊ ምክክር እያካሄደች ትገኛለች።
በምክክር ጉባዔው ማስጀመሪያ ላይ የተገኙት የናይጄሪያ የቀድሞው ፕሬዝዳንት እና በአፍሪካ ኅብረት የምሥራቅ አፍሪካ ልዩ መልዕክተኛ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በታሪካዊው ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ግብዣ ስለተደረገላቸውም አመስግነዋል። ይህ ሀገራዊ ምክክር ለኢትዮጵያ፣ ለኢጋድ እና ለአፍሪካውያን ሁሉ ታሪካዊ መኾኑን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ሀገራዊ ምክክሩን በማስጀመር ላሳዩት አርቆ አሳቢነት፤ ድፍረት እና አርበኝነት አመስግነዋል።
በናይጀሪያ እና ኢትዮጵያ መካከል መመሳሰሎች እንዳሉም ገልጸዋል። በሁለቱ ሀገራት የእርስ በርስ ግጭት አለብን ያሉት ኦባሳንጆ “የእርስ በእርስ ግጭት ከውጭ ጠላት ጋር ከመዋጋት በላይ ጎጅ ነው” ብለዋል።
በውጭ ጦርነት አሸናፊ አለ፤ የውስጥ ግጭት ግን አብሮ መያያዝ እና መውደቅ ነው ብለዋል።
በሀገራችን ከጦርነቱ በፊት ፖለቲካን ለማስቀጠል ሁሉንም ዓይነት ጥረት አድርገን ነበር፤ ማሳካት አልቻልንም፤ ወደ ጦርነት ውስጥ ገብተናል ነው ያሉት። ከወንድሞቻችን እና ከእህቶቻችን ጋር የተለየ ግንኙነትን በመፍጠር፤ ዓለም አቀፍ ታዛቢዎችን በመጋበዝ የእርስ በርስ ጦርነትን እንዲታዘቡ በሀገራችን ጋብዘን ነበር ብለዋል።
ሀገሪቱ ከገጠማት ጦርነት በኋላ ማንም አሸናፊ እና ተሸናፊ የለም የሚል ፖሊሲ በማስቀመጥ፤ የእርስ በርሰ እርቅን፣ መስማማትን በማስቀደም መልሶ መቋቋም አድርገን ነበርም ብለዋል።
አሁን ላይ በሀገራቸው “ጦርነቱ አብቅቷል የፖለቲካ ማብቂያው ውይይት ነው” በማለት በመሰባሰብ፤ ተቃዋሚዎችን እንደ ጠላት ባለማየት፤ መልሶ ወደ ጠላት አመራር ባለመላክ፤ የሥልጣን ተሳታፊ እንዲኾኑ በማስቻል መፍትሔ አስቀምጠው እንደነበር አስታውሰዋል።
በሀገራችን የፖለቲካ ውይይቶች እና ሀገራዊ ምክክሮች እንዲካሄዱ ኮሚቴዎችን በማቋቋም ሠርተናል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ዛሬ እየሠራችው ባለችው ተግባርም ጥንካሬን እና ዕድልን ተመልክቻለሁ ነው ያሉት። ታሪክ፣ ብዝሃነት፣ ያለፉ ታሪካዊ ልምዶቻችሁ፤ የአፍሪካ መዲና መኾናችሁ እና ሕዝቦቻችሁ የኢትዮጵያውያን ጥንካሬ አካል ናቸው ብለዋል።
ታሪክ ድል ይሰጣችኋል፤ ሕዝብ ዕድል ይሰጣችኋል፤ ትልቁ ድል ደግሞ ኢኮኖሚ ነው ብለዋል። ከሦስት ዓመታት በፊት ይች ሀገር በስንዴ ራሷን እንደምትችል ተናግረው ነበር አሁን አሳክተውታል ነው ያሉት።
አፍሪካውያን በዩክሬን እና በራሽያ መንጠልጠላችን አናውቅም ነበር ዛሬ ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት ራሷን ችላለች፤ ከመቻልም አልፎ ለሌሎች እየላከች ትገኛለች ነው ያሉት።
በምግብ የአፍሪካ ምንጭ መኾን ትልቅ ዕድል መኾኑንም ተናግረዋል። ሀገራዊ ምክክር ከሌለ እና የታቀደለትን ዓላማ ካላሳካ ስኬት አይኖርም ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ላደረገው አስተዋጽኦ አመስግነዋል። ቀደም ብለው ሀገራዊ ምክክሩን ጎብኝተው እንደነበርም አንስተዋል።
#አሚኮ_ዜና#ሀገራዊ_ምክክር#ኢትዮጵያ 🇪🇹 #ባሕር_ዳር_ሐምሌ_8_2018_ዓ_ም
ዘጋቢ:-ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
