“ግጭት እና ስቃይ ማብቃት አለበት!” ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ.ር)

4
🇪🇹
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባዔ እየተካሄደ ነው። በጉባዔው መክፈቻ ላይ የተገኙት የኢጋድ ዋና ጸሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ.ር) በዓለም ታሪክ ውስጥ በግጭት የተሠራም ኾነ በግጭት ያተረፈ ሀገር የለም ብለዋል። የተሻሉ የሚባሉ ሀገሮች ከሁሉም በላይ ሀገራቸውን ስላስቀደሙ፣ ስለተደማመጡ እና ስለተነጋገሩ የተሻለ ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ማንነቷን የምትፈልግ አዲስ ሀገር አይደለችም፤ በምድር ላይ ካሉ እጅግ ጥንታዊ እና ጠንካራ ሥልጣኔዎች አንዷ ነበረች ነው ያሉት። በታሪካችን እና በባሕላችን ውስጥ በጥልቀት ስር የሰደዱ እና እጅግ ውብ የኾኑ የእርቅ ሥርዓቶች ብለዋል።
ሽማግሌዎቻችን በጥበብ የታደሉ ናቸው፤ ኢትዮጵያ የራሷን ቁስል የምታክምበት ቁልፍ በእጇ ላይ አለ ነው ያሉት። መልስ ፍለጋ ለችግሮቻችን ወደ ውጪ የምናማትርበት ጉዳይ የለም ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን ችግሮችን መፍታት ብቻ ሳይኾን ለአፍሪካ እና ከዚያ በላይ መፍትሔ የሚኾን ሀገራችንን የገነባንበት፣ ሀገራችንን ያጸናንበት በርካታ ምሳሌዎች በእጃችን ያለን ሕዝቦች ነን ነው ያሉት።
የዛሬው ቀን በፖለቲካ ባሕላችን ውስጥ መሠረታዊ የለውጥ ነጥብ መኾን አለበት ብለዋል። በፖለቲካዊ ሕይወት ውስጥ የተለመደ የሚባለውን ነገር እንደገና የምንተረጉምበት መኾን አለበትም ነው ያሉት።
በማንኛውም የተለየ ማንነት ባለው ማኅበረሰብ ውስጥ በአሥተዳደር፣ በሀብት ክፍፍል እና በውክልና ዙሪያ የተለያዩ አመለካከቶች መኖራቸው የተለመደ ነው፤ ነገር ግን መሠረታዊ ስህተት የሚኾነው እና ዛሬ በዚህ አዳራሽ ውስጥ ተመካክረን ውድቅ ልናደርግ የሚገባን ልዩነቶቻችንን በኅይል ለመፍታት የሚደረጉ ጥረቶችን ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን ልዩነቶቻቸውን በብዕር ኃይል፣ በውይይት እና በጋራ መከባበር መፍታት እንደሚችሉ ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ የምናሳይበት ሊኾን ይገባልም ነው ያሉት።
“የኢትዮጵያ ታሪክ ወደፊት የሚሠራው በመነጋገር ነው፤ የኢትዮጵያ እናቶች፣ አባቶች፣ ወጣቶች እና ሕጻናት ዛሬ እናንተን እየተመለከቱ ነው፤ የሚመለከቷችሁ በተስፋ መቁረጥ ስሜት ሳይኾን በጉጉት እና በታላቅ ተስፋ እንደኾነም ገልጸዋል።
“ግጭት እና ስቃይ ኢትዮጵያ ውስጥ ማብቃት አለበት”። እንኳን ለራሳችን ለአፍሪካ ተምሳሌት የኾነ የነጻነት ቀንዲል ሀገር ነን፤ ሁሉንም ጉዳዮች ዛሬ እንደጀመርነው በውይይት እና በመነጋገር መፍታት ይቻላል፣ ይገባልም”ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“ሽምግልና፣ ንግግር እና ይቅርታ ኢትዮጵያን አጽንተው ያቆዩዋት እሴቶች ናቸው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)