“ሽምግልና፣ ንግግር እና ይቅርታ ኢትዮጵያን አጽንተው ያቆዩዋት እሴቶች ናቸው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)

5
ታሪካዊው የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በአዲስ አበባ ከተማ መካሄድ ጀምሯል። በመክፈቻ መርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ኢትዮጵያ ታሪክ ጠገብ እና ጥንታዊ የኾነች ሀገር ናት ብለዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ በታሪክ በርካታ ችግሮችን እና መከራዎችን አሳልፈናል ብለዋል። ይህንን መከራ ወደ ዕድል በመቀየር ልጆቻችን ከእኛ የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት። ሀገራዊ ምክክሩንም ሁሉም እንደ እድል ሊጠቀምበት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ጉባኤው በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ በስፋቱ፣ በአካሄዱ፣ በወሰደው ጊዜ እና በሚያስገኘው ውጤት የገዘፈ ዓላማ ያለው ለአፍሪካ ተምሳሌት የሚኾን ነው ብለዋል።
እያንዳንዷን አጋጣሚ እንደ ስጦታ በመጠቀም ወደ እድል በመቀየር ለኢትዮጵያ ብልጽግና መሠረት ለመጣል ደከመን ሰለቸን ሳንል እንተጋለንም ነው ያሉት።
በታሪካችን ስንገነባ እያደፈጡ ስንጨቃጨቅ ጊዜ ጠብቀው እንደ ሽብልቅ ጣልቃ እየገቡ መሻቶቻችንን እንዳንከውን የሚያደርጉ ኀይሎች አሉ ብለዋል። ቀይ ባሕርን ያጣንበት የታሪክ አጋጣሚ የዚህ የሽብልቅ ጉዞ ማሳያ መኾኑንም ጠቅሰዋል።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ለሚያንዥብቡ ኀይሎች ለሺህ ዓመታት ጸንታ የኖረችው ኢትዮጵያ ጥቅሟን አሳልፋ ትሰጣለች ማለት ከንቱ ምኞት ነው ብለዋል።
ሽምግልና፣ ንግግር እና ይቅርታ ኢትዮጵያን አጽንተው ያቆዩዋት እሴቶች መኾናቸውንም ገልጸዋል። በኢትዮጵያ ሽምግልና በዋርካ ይመሠላል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በይቅርታ፣ በንግግር፣ ሽምግልና እና በጋራ መቆምን በማጽናት የተሻለች ኢትዮጵያን ለልጆቻችን እናውርስ ብለዋል።
ምክክሩ ዛሬን ሳይኾን ነገን ዘልቆ የሚሄድ እና ውጤታማ እንዲኾን ተሳታፊዎች የሚያደርጉት ውይይት ከዚህ አዳራሽ ወጥቶ በመላው ኢትዮጵያ የሚያበራ መኾን ይኖርበታል ነው ያሉት።
ምክክሩ ለመላው ኢትዮጵያውያን እረፍት የሚያመጣ፣ ለአፍሪካም ተምሳሌት የሚኾን ውጤት እንዲያመጣ የምክክሩ ተሳታፊዎች የበኩላቸውን ጥረት እንዲያደርጉም አደራ ብለዋል።
የምክክር ጉባኤው ተሳታፊዎች ለዛሬ ሳይኾን ለነገ፣ ለእናንተ ሳይኾን ለልጆቻችሁ፣ ለእኔ ሳይኾን ለእኛ፣ ለሰፈር ሳይኾን ለኢትዮጵያ ብላችሁ ተመካከሩ ሲሉ አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ:-አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“በምክክሩ ታላቋን ኢትዮጵያ ማዕከል እናድርግ” ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ታላቁ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባዔ መካሄድ ጀምሯል።
Next article“ግጭት እና ስቃይ ማብቃት አለበት!” ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ.ር)