
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መሥፍን አርዓያ ለአራት ዓመታት ረጅም ጉዞ መደረጉን ተናግረዋል። 11 ኮሚሽነሮች ተሰይመውልን በብዙ ትጋት እና ድካም ከባለሙያዎች፤ ከድጋፍ ሰጭ ባለሙያዎች እና ከመላው ኢትዮጵያውያን ጋር እዚህ ደርሰናል ነው ያሉት በጉባኤው ማስጀመሪያ ባደረጉት ንግግር።
ጉባዔው የሀገርን የፖለቲካ እና የማኅበራዊ ግንኙነት አቅጣጫ የሚያቀና፤ ለቀጣዩ ትውልድ ጠንካራ እና አሥተማማኝ ሀገር ለመገንባት የሚያስችል አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የሚከፍት እንደኾነ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የረዥም ዘመን ታሪክ፤ የሚያኮሩ ባሕሎች፤ የብዝሃነት ውበት ባለቤት ብትኾንም ይህንን ታላቅነቷን በዘላቂነት ለማስቀጠል እንቅፋት በኾኑ በርካታ የሀሳብ ልዩነቶች እና አለመግባባቶች ውስጥ ማለፏንም ተናግረዋል።
ለዘመናት የዘለቁ የፖለቲካ እና የሥርዓት ጥያቄዎች ዛሬም ድረስ የዜጎችን ሰላም እና የሀገርን አንድነት እየፈተኑ ይገኛሉ ብለዋል።
ልዩነት ችግር አይደለም ያሉት ኮሚሽነሩ ችግር የሚኾነው በምክክር ፈንታ በግጭት፤ በመገለል እና በኩርፊያ እንዲሁም በኃይል ለመፍታት ሲሞከር እንደኾነም ገልጸዋል።
ሥር የሰደዱ ችግሮችን በኃይል፤ በጊዜያዊ ማስታገሻዎች እና በአግላይ ሂደት በዘላቂነት መፍታት እንደማይቻል ታሪክ አስተምሮናል ነው ያሉት።
መፍትሔው ታማኝ፤ አካታች፤ ግልጽ እና ሳይንሳዊ የኾነ ሀገራዊ ምክክር ማድረግ ብቻ እንደሆነ ገልጸዋል። ብዝኀነትን የምናጠፋበት ሳይኾን ልዩነታችንን በሠለጠነ መንገድ ይዘን በጋራ መኖር የምንችልበትን ሥርዓት የምንዘረጋበት ነው ብለዋል።
የዛሬው ጉባዔ እርስ በእርስ እንድንደማመጥ፤ የሌላውን ሕመም እንድንረዳ፤ በየጊዜው የሚያመረቅዙ ትርክቶችን እና የታሪክ ጠባሳዎች እንዲሽሩ ለማድረግ በጋራ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ እንድንስማማ ትልቅ ዕድል የሚፈጥር ሀገራዊ ፈውስ የሚካሄድበት መኾኑንም ተናግረዋል።
የሀገርን እጣ ፈንታ የሚወስኑ፤ በመሠረታዊ የሀገር ግንባታ ጉዳዮች ላይ መግባባት፤ ለዘመናት ሲያጋጩ የነበሩ ጉዳዮች ላይ የጋራ መፍትሔ በማስቀመጥ ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት ማስፈን ይጠበቃል ነው ያሉት።
በዜጎች እና በመንግሥት በልዩ ልዩ ፖለቲካ ኃይሎች ጠንካራ እምነት መገንባት፤ ወደ ፊት የሚገጥሙ የሀሳብ ልዩነቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት የውይይት እና የምክክር ባሕልን መትከል ይጠበቅብናል ብለዋል።
ከጠበበ የቡድን እና የግል ፍላጎት በመውጣት ለሀገር ሰላም እና ለቀጣዩ ትውልድ ዕጣ ፈንታ በሆደ ሰፊነት እና በሀቀኝነት መምከር ይገባል ነው ያሉት። “ታላቋን ኢትዮጵያ ማዕከል እናድርግ” ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
