
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሀገራዊ የምክክር ጉባኤውን እያካሄደ ነው። በምክክር ጉባኤው መክፈቻ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እና ሌሎችም ከፍተኛ መሪዎች እንዲሁም የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች ተገኝተዋል።
በምክክር ጉባኤው ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ ተገኝተው መልእክት ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ይህ ጉባኤ በቀላሉ የማይደግም፣ በስፋቱ፣ በአካሄዱ እና በሚያስገኘው ውጤትም በእጅጉ የገዘፈ ነው ብለዋል። በአፍሪካም ለብዙዎች ምሳሌ የሚኾን ውይይት እና ምክክር ሁሉን አቀፍ መድረክ ስለመኾኑም ገልጸዋል።
የዛሬው የምክክር መድረክ የታሪክን፣ የአጋጣሚን እና የእድልን ጠቃሚነት በውል በመያዝ ሀገርን የሚገነባ መሆኑንም ገልጸዋል። ለዘመናት የሚታወስ ታሪክ መጻፍ እድል የሚሰጥ ስለመኾኑም ገልጸዋል።
ይህ አይነት እድል በታሪክ አጋጣሚ አንዴ እንጅ ደጋግሞ የሚገኝ እድል አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን የምክክር ጉባኤ በታላቅ አክብሮት ልንተገብረው እንደሚገባ መልእክት አስተላልፈዋል።
ሁሉም ችግር በውስጡ መፍትሔ አለው፣ በርከት ያሉ ችግሮች አሳልፈናል፤ ያልተገቡ መከራዎችን አይተናል፤ ነገር ግን ፈተናዎችን በምክክር ወደ እድል ከቀየርን ልጆቻችን ከኛ የተሻለ ብልጽግና እና የኑሮ ዘየ ይኖራቸዋል ነው ያሉት።
