
የኮሪደር ልማት የኢትዮጵያን የከተሞች የጉስቁልና ዘመን ቀይሯል፤
ከደብዛዛ ወደ ማራኪ እይታ አሻግሯል፤ ልምላሜ የናፈቃቸው የአስፋልት ዳር መንገዶች 
የአረንጓዴ ካባ ለብሰዋል።የከተሞች የጨለማ ጉዞ አክትሞ
የኮሪደር ልማት ለከተሞች ውበትን ከመሥጠት ባሻገር የሥራ ባሕልን ቀይሯል፤ የአመለካከት ለውጥን አምጥቷል። መሠረተ ልማቶች በፍጥነት ሲጠናቀቁ ማየት በኮሪደር ልማት እውን ኾኗል።
የትናንት ታሪክን ከዛሬ በማስተሳሰር፤ የአካባቢን ጸጋ በማስተዋወቅ፤ የቱሪዝም ቀልብ የሚስቡ ከባቢዎችን በመፍጠር
የኮሪደር ልማት ትውልድን ለማሥተሳሰር በሥራዎቹ ገልጧል።
የትራፊክ መጨናነቅን በማስቀረት የትራንስፖርት መሻሻል አምጥቷል፤ አረንጓዴ ከባቢዎች፣ መናፈሻዎች፣ የሕዝብ ማረፊያዎች እና ፓርኮችን አሥፍቷል፤
የመሠረተ ልማት ዘመናዊነትን ፈጥሯል፤ የሕዝብ ጤና እና የአኗኗር ዘይቤን ለውጧል፤ የከተማ ብክለትን በመቀነስ በኩል ጎልህ ሚና እየተወጣ ነው።
ሥራ በቀን ብቻ ሳይኾን ሌሊትም መሥራት እንደሚቻል አሳይቷል። በመተባበር በቅንጅት መሥራት ውጤታማ እንደሚያደርግም አመላክቷል።
በአንዳንድ አካባቢዎች ከኮሪደር ልማት ጋር የሚሠሩ ኢኮ ሪዞርቶች ደግሞ ከተሞችን ይበልጥ ለጎብኝዎች ምቹ ሁኔታን እንዲፈጥሩ አድርጓል።
የኢትዮጵያ የኮሪደር ልማት በከተማ ብቻ አልተወሰነም ወደ አርሶ አደሮች ቀዬ ተሻግሯል። አርሶ አደሮች ጽዱ የመኖሪያ ቤት እንዲኖረውም እያደረገ ይገኛል። አርሶ አደሮች ጽዳቱን በጠበቀ መንገድ የሌማት ትሩፋትን እንዲያሳልጡ ረድቷቸዋል።
መንገድ፣ መብራት፣ የቴሌኮም ዝርጋታ እና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን እንዲያገኙ እያደረገ ነው። ይህም የአኗኗር ዘይቤያቸውን እየቀየረ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተለያዬ ጊዜ እንደገለጹት ኮሪደር ልማት ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና አካባቢያዊ ግቦች እንዳሉት አንስተዋል።
ቋሚ የሥራ ዕድልን በመፍጠር፤ የዕውቀት ሽግግር ልምድን በመሥጠት፤ ውብ የቤት ግንባታን በማሳለጥ፤ አማራጭ መንገዶችን በመዘርጋት የትራፊክ መጨናነቅን በመቅረፍ እና ሌሎች ተግባራትን በማሳለጥ ጠቀሜታው የጎላ መኾኑን ገልጸዋል።
በከተማ የኮሪደር ልማት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ዜጎችን ቤት በመሥራት ተጠቃሚ ለማድረግ ተሠርቷል ነው ያሉት።
በከተሞች የታየውን ለውጥ በማስቀጠል የገጠር የኮሪደር ልማትን በማፋጠን የአርሶ አደሮችን የአኗኗር ዘይቤ ለመቀየር እየተሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
አርሶ አደሮች ዘመናዊ አኗኗርን እንዲላመዱ ከማድረግ ባሻገር 

የሌማት ትሩፋቶችን የሚያለማበት እና ውጤታማ የሚኾንበትን መንገድም መፍጠር እንደተቻለ አንስተዋል።
በያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
