
አንድ ሀገር እንደ ሀገር ሊቀጥል የሚችለው የጋራ ትናንት እና የጋራ ዛሬ እና የጋራ ነገ ሲኖረው ነው። በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ትልቁ ፈተና የጋራ ትርክቶች መላላት እና በቡድናዊ ጥቅሞች መተካታቸው ነው።
የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ፍልስፍና መምህር ሀሳቡ ተስፋ የወል ትርክት የአንድ ማኅበረሰብ በጋራ ዓላማ እና ራዕይ የመቆም እሳቤ እንደኾነ ነግረውናል። መሠረቶቹም የጋራ እሴቶች፣ የክፉም ኾነ የበጎ የጋራ የትናንትና ትዝታዎች፣ የጋራ ድል ታሪኮች (እንደ ዓድዋ፣ የሕዳሴው ግድብ፣ ላሊበላ፣ አክሱም፣ ጀጎል እና እንደ ፋሲል ቤተመንግሥት ያሉ የሥልጣኔ እና የርብርብ ውጤቶች)፣ የወደፊት የጋራ ሕልም እና ራዕዮች ናቸው ብለውናል።
የጋራ ትርክት የሌለው አካል የጋራ ትናንት፣ ዛሬ እና ነገ የለውም፤ የጋራ ነገ የሌለው ሀገር ደግሞ እንደ ሀገር ሊቀጥል አይችልም ነው ያሉት።
አሁን ላይ ሀገራዊ ጥቅም እና ቡድናዊ ጥቅሞች ተጋጭተው ለኢትዮጵያ ትልቅ ዳፋ ይዘው መምጣታቸውንም አንስተዋል። ለዚህም አንዱ ምክንያት የታሪክ ሽሚያ እና ፖለቲካዊ ቁርሾ ነው ብለዋል። ታሪክን ለዛሬ እና ለነገ መማሪያ ከማድረግ ይልቅ የቡድን የፖለቲካ ፍላጎትን ለማሳካት እና ተበዳይነትን አጉልቶ ለማሳየት እንደ መሣሪያ የመውሰድ ሁኔታ እንዳለም ጠቅሰዋል።
የዜግነት እና የቡድን ማንነት ፉክክር ሌላኛው ጉዳይ መኾኑን ገልጸዋል። የጋራ ሀገራዊ ማንነት እየመነመነ የቡድን ማንነቶች እየገነኑ መምጣታቸውንም አመላክተዋል። ይህ ደግሞ በቡድኖች መካከል ውጥረት እና መፋጠጥን በመፍጠር ሀገራዊ ራዕይን እያናጋ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ወሳኝ የታሪክ እጥፋት ላይ እንደምትገኝም አንስተዋል። የትናንት ችግሮች ተከማችተው ዛሬ ላይ ደርሰዋል፤ እነዚህን ችግሮች ደግሞ ለቀጣዩ ትውልድ ማሻገር አይገባም ነው ያሉት። ሀገራዊ ምክክሩ ወደ ነገ መሻገሪያ ብቸኛው ድልድይ መኾኑንም አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያውያንን ወደ አለመግባባት እየወሰዱ ያሉ ችግሮች ሀገር በቀል ናቸው ያሉት መምህሩ በራሳችን የተፈጠሩ ችግሮችን መፍታት የሚቻለው በራሳችን በምናደርገው ሀገራዊ ምክክር እንደኾነም ጠቁመዋል። ካልተነጋገርን ከእነ ችግሮቻችን መቀጠል አንችልምም ብለዋል። ያለፈውን ታሪክ ዛሬ ልንኖረው አንችልም፤ ነገር ግን ተምረንበት ዛሬን እና ነገን የተሻለ ለማድረግ መሥራት ይገባል ብለዋል። ብሔራዊ ምክክሩ ደግሞ ለዚህ ትልቅ ምቹ ሁኔታ መኾኑን ተናግረዋል።
ጸጋ እያላት ግን ባለመግባባት በተቸገረች ሀገር ላይ መጨከን ዳተኝነት ነው፤ ስለዚህ በምክክሩ ሂደት ውስጥ የመሻገሪያ ድልድይ መገንባት ግድ ይላል ብለዋል።
መምህር ሀሳቡ አሁን ያሉ አብዛኞቹ ችግሮች ማኅበረሰብ ወለድ ሳይኾኑ ሊቅ (ምሁር) ወለድ ናቸው፤ ምሁራን ሚናቸውን ሊቀይሩ ይገባልም ብለዋል። በማኅበረሰቡ ውስጥ መከፋፈልን የሚያመጡ ጎታች ሀሳቦችን መተው ተገቢ እንደኾነም አስገንዝበዋል። ታሪክን የቁርሾ መነሻ ከማድረግ ወጥተው አንድነት እና እኩልነትን የሚያሰፍን የትርክት ማሻሻያ ማድረግ እንደሚገባም ገልጸዋል።
ማኅበረሰቡን የሚነጥል አካሄድን በማረም፣ አሰባሳቢ ታሪኮችን አጉልቶ ወደፊት ማምጣት እና ለሕዝቡ መንገድ መኾን እንደሚገባም መክረዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎት እና ቁጥር እየሰፋ ስለመጣ ከጥቅሞች እና ከጋራ ራዕይ አንጻር ታሪክን እየቃኙ የወል ትርክት ከትናንት የተሻለ ፋይዳ እንዲኖረው ማድረግም ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ጠቅሰዋል።
በተለያየ መንገድ የተሰባበሩ የጋራ ትርክቶችን ጠግኖ ሀገርን ወደፊት ለማራመድ መጀመሪያ የችግሩን ምንጭ መረዳት፣ ከዚያም በሀገራዊ ምክክሩ የጋራ መፍትሔ ማምጣት፣ የመኖር እና ያለመኖር ጉዳይም ነው ብለዋል።
#ባሕር_ዳር:ሐምሌ 07/2018 ዓ.ም
በሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
