ሕግ ማስከበር ለማኅበረሰብ ሰላም፣ ዕድገት እና ህልውና ወሳኝ ሚና እንዳለው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ገለጹ።

6
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የሕግ ማስከበር እና ሰላም ማረጋገጥ በተመለከተ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ለከተማዋ መሪዎች ባስተላለፉት መልዕክት ሕግ ማስከበር ለማኅበረሰብ ሰላም፣ ዕድገት እና ህልውና ወሳኝ ሚና እንዳለው አስገንዝበዋል።
ከንቲባው በንግግራቸው ያነሱት ዋና ዋና ነጥቦች፦
የሕግ የበላይነት እና እኩልነት፦ ሕግ በሁሉም ሰው ላይ እኩል ተፈጻሚ መኾን እንዳለበት እና ይህም “ከሕግ በላይ ማንም የለም” የሚለውን መርህ እንደሚያረጋግጥ ገልጸዋል።
የኢኮኖሚ እና ኢንቨስትመንት እድገት፦ ሰላምና መረጋጋት በሰፈነበት ሀገር ውስጥ የሀገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስተሮች በነጻነት ለመሰማራት እንደማይሰጉ አብራርተዋል። ንብረትና ውል በሕግ ጥበቃ እንደሚደረግላቸው ሲያውቁ ኢኮኖሚው እንደሚያድግ፣ የሥራ ዕድል እንደሚፈጠር እና የሰብዓዊ መብቶችም እንደሚከበሩ ጠቁመዋል።
የታቀደ አመራር አስፈላጊነት፦ ሰላም ማረጋገጥና ሕግ ማስከበር ለተረጋጋ ልማት እና ለመልካም አሥተዳደር መፈጠር ያለውን ጉልህ አስተዋጽኦ በመገንዘብ አቅዶ መሥራት ዋነኛ ጉዳይ መኾኑን አሳስበዋል።
የባሕር ዳር ስትራቴጂካዊ ፋይዳ፦ ባሕር ዳር በፈጣን ዕድገት ላይ የምትገኝ፣ የሁሉም የልማት እና የቱሪዝም አውታሮች ማዕከል መኾኗን በመገንዘብ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ እና ሕግ እንዲከበር በትኩረት መረባረብ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በመጨረሻም አቶ ጎሹ እንዳላማው በየደረጃው የሚገኘው የጸጥታ መዋቅር እና አመራር ከመላው ማኅበረሰብ ጋር በመቀናጀት ሕገ-ወጥነትን መከላከል እንዳለበት አሳስበዋል። የሕግ ማስከበር ሥራዎችን በተጨባጭ በመፈጸምም ሙሉ በሙሉ ወደ ተቀናጀ ልማት በመዞር ፈጣን ለውጥ ማምጣት እንደሚገባም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየሥልጣን ምኞት እና የሕገ ወጡ የሕወሃት ቡድን ያላባራ የጦርነት ፍላጎት
Next articleየወል ትርክት፣ ሀገራዊ ምክክር እና የነገዋ ኢትዮጵያ እጣ ፈንታ