የሥልጣን ምኞት እና የሕገ ወጡ የሕወሃት ቡድን ያላባራ የጦርነት ፍላጎት

10
⚔️
40 መጻሕፍትን እና ከ400 በላይ በሚኾኑ ምሁራዊ ጽሑፋቸው የሚታወቁት እና በለንደን ኪንግስ ኮሌጅ የጦርነት ጥናቶች ክፍል የዓለም አቀፍ የፖለቲካ ጽንሰ-ሀሳብ ተማራማሪው ፕሮፌሰር ሪቻርድ ኔድ ሌቦው እ.አ.አ. ከ1648 ጀምሮ የተደረጉ 94 ዓለም አቀፍ ጦርነቶችን መርምረዋል።
 “ሀገራት ለምን ወደ ጦርነት ይገባሉ”? በሚለው መጽሐፋቸው አብዛኞቹ ጦርነቶችን በተመለከተ ጥናቱ መሪዎችን ተወቃሽ ያደርጋል።
ፕሮፌሰሩ በጥናታቸው፦
👉58 በመቶ የሚኾኑት ጦርነቶች የክብርና የደረጃ ፍለጋ ውጤቶች ናቸው የሚል ነው።
👉 18 በመቶው ለደኅንነት ሲባል ይደረጋሉ ይላል በዚሁ ጥናት።
👉 10 በመቶው ደግሞ ለበቀል ይካሄዳሉ ነው የሚለው።
👉 ቀሪው ሰባት በመቶ ለቁሳዊ ጥቅም የሚደረጉ እንደኾኑ በጥናቱ ላይ በዝርዝር ተቀምጠዋል። መሪዎች ግን ለጦርነቶቻቸው ሁልጊዜም ምክንያታዊ ሽፋን ይሰጣሉ፤ ነገር ግን ከውስጥ ያለው እውነተኛ ገፊ ምክንያት የተጎዳ ኩራት ነው ሲሉም አብራርተዋል።
ይህን ጽንሰ ሀሳብ ሕገ ወጡን የሕወሃት ቡድን በሚገባ ይገልጻል። ሕገ ወጡ ሕወሃት በ2010 ዓ.ም ከመንበረ ሥልጣኑ ወርዷል፤ በ2013 ዓ.ም ደግሞ አውዳሚ ጦርነት ከፍቷል። ይህ ጦርነት ለዓመታት ቆይቷል። በኋላም በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት ተኩስ ቆሞ እንደነበር ይታወሳል።
አሁን ደግሞ ዳግም ወደ ጦርነት ለመግባት ሕገወጡ ሕወሃት ዝግጅት ላይ መኾኑ እየተነገረ ይገኛል። ይህን የፖለቲካ ውጣ ውረድ በሌቦው ጥናት መተንተን ትክክለኛ ዕይታን ይሰጠናል።
ሕገ ወጡ ሕወሃት ለሩብ ምዕተ ዓመት በላይ የሀገሪቱ ፖለቲካ ፍጹም የበላይ ነበር። ይህን የሥልጣን ከፍታ ማጣቱ የቡድኑን መሪዎች ኩራት እና ክብር ክፉኛ ነክቶታል። የ2013 ጦርነት ዋነኛ መንስኤ ይህ የጠፋውን ክብር የማስመለስ ፍላጎት ነበር ማለት ይቻላል።
መሪዎቹ የበላይነታቸውን ዳግም ለማረጋገጥ ሲሉ ጦርነት መርጠዋል። ቡድኑ ጦርነቱን የሕልውና እና የደኅንነት ጉዳይ አድርጎ አቅርቦታል። ነገር ግን ሌቦው እንዳሉት ጦርነትን ለማካሄድ የተሰጠ ምክንያታዊ ሽፋን ነው። የጦርነቱ እውነተኛ ሞተር የመሪዎቹ የሥልጣን ጥማት እና ያጡትን ደረጃ የመመለስ ፍላጎት ነው።
ከማዕከላዊ ሥልጣን ሲገፉ የተሰማቸውን መዋረድ በበቀል ለመመለስ ሞክረዋል። ማዕከላዊ ሥልጣን ማጣት የሀገርን ሀብት ማጣትንም ያካትታል። ይህ ቁሳዊ ጥቅም ሌላኛው የጦርነት ገፊ ምክንያት ኾኗል።
አከራካሪ የኾኑ የድንበር እና የመሬት ጉዳዮች ሕዝቡን ለጦርነት ለማነሳሳት ዋነኛ መነሻዎች ናቸው። በውጫዊ ገጽታቸው እነዚህ የቁሳዊ ጥቅም እና የደኅንነት ጉዳዮች ይመስላሉ። ከስረ መሰረቱ ግን የግልን ኩራት እና ታሪካዊ ስም የማስጠበቅ ጉዳይ ነው። መሪዎቹ የገጠማቸውን የፖለቲካ ሽንፈት እና ውርደት በቀጥታ ወደ ማኅበረሰቡ ያወርዳሉ፤ ተከበናል የሚል የበቀል ስሜት ይፈጥራሉ። በዚህም የራሳቸውን የቆሰለ ኩራት ለመጠገን አዲስ ትውልድን ለጦርነት ያዘጋጃሉ።
ከፕሪቶሪያ ስምምነት በኋላም መሪዎቹ የቆሰለ ኩራታቸውን ሙሉ በሙሉ አላከሙም። መሪዎቹ አሁንም ሕዝብን ለማሳመን ሲጥሩ ይስተዋላሉ።
የሕዝብ ሕልውና ወይም ራስን በራስ ማሥተዳደር ሲሉ ይደመጣሉ። እውነታው ግን ከሥልጣን መውረድ የፈጠረው ሥነ ልቦናዊ ስብራት ነው።
የፖለቲካ ተቋማት የራሳቸው ስሜት የላቸውም። የሚመሯቸው ሰዎች ግን በስሜት፣ በጥቃቅን ፍላጎት እና በበቀል ይነዳሉ። የሕገ ወጡ የጦርነት አዙሪትም የዚሁ የተጎዳ ኩራት እና የሥልጣን ጥማት ግልጽ ማሳያ ነው።
በአጠቃላይ ግን በጦርነት ከሚሞቱት ሰዎች መካከል 90 በመቶ የሚኾኑት ምንም የማያውቁ ንጹሐን እንደኾኑ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያስረዳል። በዚህም ጦርነት የሰው ልጅ በምክንያታዊነት የማሰብ አቅሙን ማጣቱን የሚያሳይ አሳዛኝ ክስተት መኾኑን ታዋቂው ጸሐፊ ጆን ስታይን ቤክ “ማንኛውም ጦርነት የሰው ልጅ የመውደቁ ምልክት ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
✍️ ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“ኢትዮጵያ በታላቅ የድል ዋዜማ ላይ ናት” የጠቅላይ ሚኒስትሩ የታሪክ አደራ ጥሪ!
Next articleሕግ ማስከበር ለማኅበረሰብ ሰላም፣ ዕድገት እና ህልውና ወሳኝ ሚና እንዳለው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ገለጹ።