የኮሌራ ወረርሽኝ ሥጋት ነውን?

7
ባሕር ዳር: ሐምሌ 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በክረምት ወቅት ከሚከሰቱ የጤና ስጋቶች አንዱ የኮሌራ ወረርሽኝ ነው። በዚህ ወቅትስ በተለይ በአማራ ክልል ኮሌራ ወረርሽኝ ስጋት ነውን?
በአማራ ክልል ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የበሽታዎች እና ሌሎች ክስተቶች ቅኝት እና ምላሽ አሰጣጥ ባለሙያ ወንደወሰን የኋላው ምላሽ አላቸው።
በቋራ ወረዳ በርሚል የጸበል ቦታ የኮሌራ ምልክቶች ታይተው ነበር ያሉት ባለሙያው በተደረገው ፈጣን የመከላከል ሥራ አኹን ላይ ወረርሽኙ በቁጥጥር ሥር መዋሉን ገልጸዋል።
ነገር ግን ወረርሽኙ ስጋት በመኾኑ ዋና ዋና የሥጋት አካባቢዎች ተለይተው ክትትል እየተደረገባቸው ይገኛል ነው ያሉት።
✍️የሥጋት አካባቢዎች
#የጸበል ቦታዎች፦ ባለፉት ዓመታት ወረርሽኙ በተደጋጋሚ የታየባቸው እንደ በርሚል ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ አቡነ ሐራ፣ ወንቅሸት ገብርኤል እና ሌሎች 58 የሚኾኑ ከፍተኛ የሰው ቁጥር የሚያስተናግዱ የጸበል ቦታዎች ተለይተዋል።
#ለወቅታዊ ሥራ ሰው የሚበዛባቸው ቦታዎች፦ እንደ መተማ እና ቋራ ያሉ ለቀን ሥራ እና ለወርቅ ማውጣት ከፍተኛ የሰው ኃይል የሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች በኢንስቲትዩቱ የስጋት አካባቢ ተብለዋል።
#የውኃ እጥረት ያለባቸው አካባቢዎች፦
በዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር (በተለይም አበርገሌ) ንጹሕ የመጠጥ ውኃ ባለመኖሩ ምክንያት ኅብረተሰቡ የወንዝ ውኃን ለፍጆታ የሚጠቀምባቸው አካባቢዎች በመኾናቸው በትኩረት እየተሠራባቸው የሚገኙ ቦታዎች ናቸው ብለዋል ባለሙያው።
✍️ወረርሽኙን ለመከላከል መደረግ ያለባቸው ጥንቃቄዎች፦
​-ለመጠጥ እና ለቤት ውስጥ አገልግሎት የሚውል ውኃን በውኃ ማከሚያ ኬሚካሎች አክሞ መጠቀም።
​-ከመጸዳጃ ቤት መልስ፣ ምግብ ከመመገብ በፊት እና ታካሚዎችን ከረዱ በኋላ እጅን በውኃ እና በሳሙና በሚገባ መታጠብ።
​-በመጸዳጃ ቤት ብቻ መጸዳዳት
-ምግቦችን በደንብ አብስሎ መመገብ፤ አትክልት እና ፍራፍሬዎችን ከመመገብ በፊት በታከመ ውኃ በሚገባ ማጠብ ወይም ልጦ መጠቀም።
-የግል እና የአካባቢ ንጽሕናውን መጠበቅ ይገባል።
✍️ ስጋት ባለባቸው የጸበል ቦታዎች ላይ የሰዎች እንቅስቃሴ የተገደበ እንዲኾን እና የጥንቃቄ ትምህርት እየተሰጠ መኾኑን የበሽታዎች እና ሌሎች ክስተቶች ቅኝት እና ምላሽ አሰጣጥ ባለሙያው ወንደወሰን የኋላው ጠቁመዋል።
✍️የጉዞ ማኅበራትም ምዕመናንን ወደ ጸበል ቦታዎች ከመውሰዳቸው በፊት ከአካባቢው የጤና ቢሮ ጋር በመመካከር ተጨባጭ ኹኔታውን እንዲያገናዝቡ አሳስበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየወል ትርክት፣ ሀገራዊ ምክክር እና የነገዋ ኢትዮጵያ እጣ ፈንታ
Next articleየከተሞች የለውጥ ጉዞ፤ የኮሪደር ልማት እና የአርሶ አደሮች የዘመናዊ ሕይወት ጅማሮ