
የሥልጣን ጥመኛነቱ የሕዝብ ሰቆቃ እና ሥቃይ እንዳያደምጥ፣ የእናቶችን ሲቃ እንዳያሥተውል፣ የአባቶችን እንባ እንዳይመለከት፣ የወጣቶች ሕይወት በአጭር መቀጨቱን እንዳይገነዘብ ዓይኑን ሸፍኖታል – ሕገ ወጡን የሕወሃት ቡድን።
እርሱ ያልመራት ሀገር የጦርነት ባድማ፣ እርሱ ያልመራት ሀገር የሞት መንደር ፣ ያልመራቸው ሕዝቦቿ ደግሞ የሰላም አየር የሚተነፍሱ አይመስሉትም።
ዛሬ ላይ ስለ ኢትዮጵያ ሲናገር ሕገወጥ ቡድኑ ለ27 ዓመት በሥልጣ ላይ በቆየበት ዘመን ሀገር ሕዝቦቿ በብሔር እንዲከፋፈሉ፣ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዳይረጋገጥ፣ ጨቋኝ ተጨቋኝ የሚል የሃሰት ትርክት እንዲፈጠር፣ ኢትዮጵያ ከከፍታዋ ማማ እንድትወርድ ያደረገ አይመስለውም።
ይህ ሕገወጥ ቡድን ጽንሰቱ፣ ትውልዱ፣ ዕድገቱ እና ሞቱ በግጭት፣ በጦርነት፣ በመከፋፈል እና በሥልጣን ሽሚያ ብቻ መኾኑን ግን ዓለም ያወቀው ሀቅ ነው።
ከሥልጣን ከመውረዱ ማግሥት በ2013 ዓ.ም ጦርነትን ቀሥቅሶ ኢትዮጵያ አሸናፊ ብትኾንም ለዘላቂ ሰላም ስትል የፕሪቶሪያውን ውል እንዲፈረም ተደርጓል። የጦርነት አባዜው ያለቀቀው ሕገወጡ ቡድን ዳግም ወደ ሥልጣን ለመምጣትም የፕሪቶሪያውን ስምምነት አፍርሶ ጦርነትን እየቀሰቀሰ ነው።
ቡድኑ በተደጋጋሚ የሚደርስበትን ሽንፈት ባለመቀበል ድጋሜ ለጦርነት ተዘጋጅቷል። የሰላም ስምምነቱን እንደ ጊዜ መግዣ እና ለጥፋት መልሶ መደራጃ አድርጎታል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት የቀድሞ አፈ ጉባኤ እና የቀድሞው የሕወሃት የማዕከላዊ ኮሚቴ እና የሥራ አሥፈጻሚ አባል የነበሩት ኬሪያ ኢብራሂም ሕገወጡ ሕወሃት ትግራይን የጦርነት ማዕከል ለማድረግ፣ የወጣቶችን እና የሕዝቡን ደም ለማፍሰስ እየተዘጋጀ መኾኑን ተናግረዋል።
ለትግራይ ሕዝብን እኔ ብቻ ነው የምጠቅመው፤ እኔ ያልመራኋት ትግራይ፤ እኔ ያላሥተዳደርኳት ኢትዮጵያ በልማት ጎዳና አትራመድም፣ በዕድገት ጎዳና አትዘልቅም በማለት ዳግም ሥልጣንን ለማግኘት ጦርነትን አማራጭ ማድረጉን ገልጸዋል።
ለአፈና የሚያመቸውን፣ እናቶችን የሚያስለቅስበትን፣ ወጣቶችን ለጦርነት የሚማግድበትን አዋጅ በማጽደቅ የትግራይ ሕዝብን ዳግም እየበደለ መኾኑንም አንስተዋል።
ሕዝብ ጦርነት ይብቃ ሰላም እንፈልጋለን እያለ ጥያቄህ የሚፈታው በጦርነት ብቻ ነው በማለት አምባገነንነቱን እያራመደ መኾኑንም ገልጸዋል።
ወጣቶችን በዶላር እየሸጠ ሥልጣንን ለማግኘት እየሠራም ነው ብለዋል። ወጣት ልጆቹ ለጦርነት ሲታፈኑ የትግራይ ሕዝብ በአቅሙ ድንጋይ አንሥቶ ከሕገወጡ ሕወሃት ጋር እየገጠመ ነው ብለዋል። ዳግም ሥልጣንን ለማግኘት ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር እየሠራ እንደሚገኝም አብራርተዋል።
ሕወሃት በሥልጣን ዘመኑ ከኤርትራ እና ከሱዳን ጋር የማይስማማ እንደነበር አንሥተው እኔ ያልመራኋት ሀገር ትፍረስ በማለት አሁን ላይ ወዳጅ አድርጎ እየሠራ ነው ብለዋል። የሕወሃት ዓላማ ወደ ሥልጣን መመለስ ካልኾነም የኢትዮጵያን አንድነት በማፍረስ ማዳከም እና እንድትፈራርስ ማድረግ መኾኑንም ገልጸዋል።
ለዓመታት የዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ከማታውቅ፣ አውቃም ለመተግበር ከማትሞክር፤ ሕዝቦቿን በመከራ እና በሥደት ከምታሰቃይ ኤርትራ ጋር ተወዳጅቶ ለጥፋት እየሠራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
የሕወሃት የጥፋት ሤራን በመረዳት እና ውስጥን በማጥራት ሕገወጡን የሕወሃት ቡድን ማስወገድ ይገባል ነው ያሉት። ሤራውን መረዳት ብቻ ለውጥ አያመጣም ያሉት ወይዘሮ ኬሪያ በተግባርም በመቃወም የትግራይ ሕዝብን ሰላም እና ልማት መመለስ ይገባል ብለዋል።
#አሚኮ_ዜና #የፕሪቶሪያ_ስምምነት #ሕገወጡ_ሕወሃት #ኢትዮጵያ🇪🇹
#AMICO_News #Pretoria_Agreement #The_Illegal_TPLF #Ethiopia🇪🇹
#ባሕር ዳር:ሐምሌ 05/2018 ዓ.ም
ዘጋቢ:-ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
