
የሀረሪ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት በ2018 የበጀት ዓመት የኅብረተሰቡን የመረጃ ፍላጎት ያማከሉ እና ወቅቱን የዋጁ ውጤታማ የኮሙኒኬሽን እና የሚዲያ ተግባራት መከናወናቸውን አስታውቋል።
የጽሕፈት ቤቱ ኀላፊ ሔኖክ ሙሉነህ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ መረጃን ለሕዝብ ተደራሽ ከማድረግ ባለፈ የአፍራሽ ኀይላትን አጀንዳዎች በማምከን ረገድ አበረታች ሥራዎች መሠራታቸውን ጠቁመዋል።
በበጀት ዓመቱ የተመዘገቡ ዋና ዋና ስኬቶች ሲገልጹ እንዳሉትም የክልሉ ሕዝብ የቆየው የሰላም፣ የመቻቻል እና የአብሮነት እሴት እንዲጠናከር እንዲሁም የሀረሪ ውብ የቱሪስት መስህቦች በተለያዩ የሚዲያ አውታሮች እንዲተዋወቁ ተደርጓል።
የክልሉን መልካም ገጽታ በመገንባት በሕዝብ እና በመንግሥት መካከል ሁነኛ የመረጃ ድልድይ በመኾን የላቀ ተግባቦት መፍጠር እንደተቻለም ጠቁመዋል።
በክልሉ የሚከናወኑ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎችን ማኅበራዊ ሚዲያዎችን እና ሀገር አቀፍ መገናኛ ብዙኃንን በመጠቀም ለሕዝብ ተደራሽ ስለመደረጉም አብራርተዋል።
የሚዲያ ሞኒተሪንግ፣ የሕዝብ አስተያየት ጥናት እንዲሁም የህትመት ዝግጅት እና ስርጭት ሥራዎች በውጤታማነት ስለመከናወናቸውም ነው የጠቆሙት።
በወቅታዊ ሀገራዊ እና ክልላዊ ጉዳዮች ላይ የሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ዜናዎች፣ ዶክመንተሪዎች እና የአቋም መግለጫዎች በማዘጋጀት የኅብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ማጎልበት እና የጋራ መግባባት መፍጠር ተችሏልም ነው ያሉት።
አቶ ሔኖክ ሙሉነህ አክለውም በአዲሱ የበጀት ዓመት ተቋሙ የተቋቋመለትን ዓላማ ይበልጥ በብቃት እንዲወጣ ለማስቻል እና የኅብረተሰቡን ወቅታዊ የመረጃ ፍላጎት በላቀ ደረጃ ለማሟላት በትኩረት እንደሚሠራም አረጋግጠዋል።
#HarariCommunication #Ethiopia #MediaAndCommunication #HararTourism #Development
#ባሕር_ዳር:ሐምሌ 06/2018 ዓ.ም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
