በሳዑዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ጉዳይ የተመለከተ መግለጫ

7

 

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ፤ በሳዑዲ ዓረቢያ ውስጥ የሚገኙ የኢትዮጵያውያንን ሁኔታ በተመለከተ መግለጫ አውጥቷል።

በተለይም ደግሞ የሕግ ሒደትና የፍርድ ውሳኔ የተላለፈባቸውን ወገኖች በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ከሚመለከታቸው የሳዑዲ ዓረቢያ ባለሥልጣናት ጋር በቅርበት መሥራቱን ቀጥሏል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በውጭ አገር ለሚኖሩ ዜጎቹ ደኅንነት፣ ጥበቃና የቆንስላ ድጋፍ ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣል። በሳዑዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ በሚገኙ ዜጎች ጉዳይም መንግሥት በከፍተኛ አመራሩ በኩል ከአገሪቱ ባለሥልጣናት ጋር ተከታታይ ውይይቶች አድርጓል። በተጨማሪም በሪያድ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ እና በጅዳ በሚገኘው ቆንስላ ጄኔራል አማካኝነት፥ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ የኢትዮጵያ ዜጎች ሰብዓዊ ምሕረት እንዲደረግላቸው ለመጠየቅ፣ የቆንስላ ድጋፍ እንዲያገኙ ለማድረግና ተገቢው መፍትሔ እንዲፈለግላቸው ከሚመለከታቸው የሳዑዲ ባለሥልጣናት ጋር ያለውን ውይይት አጠናክሮ ቀጥሏል።

እነዚህ ቀጣይነት ያላቸው የዲፕሎማሲ እና የቆንስላ ጥረቶች በሰብዓዊነት ረገድ አዎንታዊ ውጤቶችን አስገኝተዋል። እስከ አሁን ድረስ በአጠቃላይ 1 ሺህ 971 ኢትዮጵያውያን የሳዑዲ ባለሥልጣናት ካደረጉት የንጉሣዊ ምሕረት ተጠቃሚ መሆን የቻሉ ሲሆን፥ የኢትዮጵያ መንግሥትም እነዚህን ዜጎች ወደ አገራቸው በተከታታይ በረራዎች እየመለሰ ይገኛል። ሚኒስቴሩ ይህንን ሒደት በቆንስላና በሰብዓዊ ጉዳዮች ላይ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ትብብርና የረጅም ዘመን ግንኙነት የሚያንጸባርቅ መሆኑን ይገነዘባል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በውጭ አገር የሚኖሩ የኢትዮጵያውያንን ጥቅሞች፣ መብቶችና ደኅንነት ለመጠበቅ ያሉትን የዲፕሎማሲና የቆንስላ አማራጮች ሁሉ መጠቀሙን የሚቀጥል ሲሆን፥ ዜጎቹን በሚመለከቱ ቀሪ ጉዳዮች ላይም ከሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት ከሚመለከታቸው ባለሥልጣናት ጋር ያለውን ግንኙነት አጠናክሮ ይቀጥላል ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

#አሚኮ #ባሕርዳር #አሚኮዜና #ኢትዮጵያ #ውጭጉዳይሚኒስቴር

#ባሕር ዳር:ሐምሌ 05/2018 ዓ.ም

Previous article⚠️የሕገወጡ ሕወሃት ቡድን የዳግም እልቂት ግብዣ
Next articleየሀረሪ ክልል ውብ የቱሪስት መስህቦች በተለያዩ የሚዲያ አውታሮች እንዲተዋወቁ ውጤታማ ሥራ ተሠርቷል። 📻📺