⚠️የሕገወጡ ሕወሃት ቡድን የዳግም እልቂት ግብዣ

10

 

የአንድ ሀገር ተተኪ ትውልድ የለውጥ፣ የዕድገት እና የብልጽግና መሠረት ነው። ባለፉት ዓመታት በትግራይ ክልል በነበረው ነባራዊ ሁኔታ ግን ያረጁ ፖለቲከኞች ተተኪ ወጣቱን ለፈጠራ እና ለሀገር ግንባታ ከማሰለፍ ይልቅ የፖለቲካ ፍላጎት ማስፈጸሚያ እና የጦርነት ማገዶ ሲያደርጉት ቆይቷል።

ሕገወጡ የሕወሃት ቡድን የያዘው አውዳሚ አካሄድ ሀገር ተረካቢውን ወጣት ወዳልኾነ አቅጣጫ በመውሰድ ያደረሰው ጉዳት ዘርፈ ብዙ ነው። የብዙዎችን ውድ ሕይወትም ቀጥፏል። አካላቸውን አጉድሏል። ንብረታቸውንም አውድሟል። ማኅበራዊ መዋቅራቸውንም አናግቷል።

ሥልጣን ባጣ ማግስት የጀመረው የትጥቅ ግጭት በሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ወጣቶችን፣ ተማሪዎችን እና ታዳጊዎችን ጭምር ወደ ጦርነት ግንባር እንዲማገዱ አድርጓል። በትምህርት ገበታቸው ላይ ኾነው የነገዋን ሀገር መረከብ የነበረባቸው ወጣቶች የጥላቻ እና የጦርነት ፕሮፓጋንዳ ሰለባ ኾነዋል። ለወጣቱ ትውልድ መጻሕፍት ከማቅረብ እና ከቴክኖሎጂ ጋር ከማገናኘት ይልቅ የጦር መሣሪያ በማቅረብ የአንድ ትውልድ መጻኢ ዕድል በጦር ሜዳ እንዲቀበር አድርገዋል። የወጣቱ ትውልድ መባከን እና ከዚህ በፊት የደረሰው ጉዳት ዛሬም አላስተማረውም። ትንኮሳውንም ቀጥሎበታል።

ለሕዝብ እንደሚቆረቆር የሚያስመስለው ቡድን ዛሬም የትግራይን እናቶች እያሳዘነ እና እያስለቀሰ ይገኛል። ሀዘኑ የትግራይ ወገኖችን በገመድ አስታጥቋል። ዘመናትን ወጥታ እና ወርዳ ባሳደገችው ልጇ ማዘዝ ያልቻለችው የትግራይ እናት እንባ ሰው ለኾነ ሁሉ ያማል። እቆረቆርለታለሁ ለሚለው ማኅበረሰብ ያልኾነ ቡድን ለማን ያዝናል?

📉በሰሜኑ ጦርነት ወቅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂውማን ራይትስ ዎች ያወጧቸው ሪፖርቶች እንደሚያስገነዝቡት ታዳጊዎች እና ወጣቶች ያለ ዕድሜያቸው በግዳጅ እና በማግባባት ለጦርነት ተዳርገዋል። በትምህርት ገበታ ላይ መገኘት ከነበረባቸው ሕጻናት እና ወጣቶች መካከል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው በጦርነቱ ምክንያት ሕይወታቸውን አጥተዋል። ለአካል ጉዳት እና ለከፍተኛ ሥነልቦናዊ ቀውስ ተዳርገዋል። ይህም ለአንድ ማኅበረሰብ የጀርባ አጥንት የኾነውን ምርታማ ኀይል ያሽመደመደ ክስተት ነው።

ዩኒሴፍ በ2014 ዓ.ም ያወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየውም በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በተቀሰቀሰው ግጭት ምክንያት ከ2 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ሕጻናት እና ወጣቶች ከትምህርት ገበታቸው ውጭ መኾናቸውን አረጋግጦ ነበር። ቡድኑ አሁንም ቢኾን ካለፉት ስህተቶቹ ከመማር ይልቅ ወጣቱን በብሔርተኝነት ስሜት በመቀስቀስ እና የሐሰት ትረካዎችን በመጋት ለሌላ የጦርነት አዙሪት የማዘጋጀት አዝማሚያዎችን እያሳየ ይገኛል። ሰላምን በዘላቂነት ከመገንባት ይልቅ የክልሉን ወጣት በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እና በጎረቤት ክልሎች ላይ በማነሳሳት የቁርሾ ፖለቲካን ማራዘምን መርጧል።

ቡድኑ ወጣቱን መሣሪያ በማድረግ የራሱን ዕድሜ ለማራዘም የሚጠቀምበት “የዳግም እልቂት ግብዣ” ስልት በቃ ሊባል የሚገባ ተግባር ነው። የሰላም ንፋስ ለኢትዮጵያ ይገባታል። ግጭቱ፣ እራቡ፣ መፈናቀሉ፣ ተጋብቶ እና ተዋልዶ የኖረው ማኅበረሰብ መለያየት፣ በጥርጣሬ መተያየት ይበቃል። የተተኪው ትውልድ ተስፋ ላይ የተደቀነው ጥቁር መጋረጃ ተከፈሎ የማለዳ ፀሐይ ትፈንጥቅ።

በተለያየ ጊዜ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ሲያደርጓቸው የነበሩ ንግግሮች እንደሚያስገነዝቡትም ወጣቱን ለሰላም፣ ለቴክኖሎጂ እና ለልማት ማዘጋጀት ሲገባ የጠመንጃ አምላኪ እና የጥላቻ ተላላኪ ማድረግ የወደፊቷን ሀገር አደጋ ላይ ይጥላል። ይህንን ትውልድ አጥፊ አካሄድ ለመግታት እና ወጣቱን ወደ ትክክለኛው የልማት መስመር ለመመለስም የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰድ ደግሞ ወሳኝ የመውጫ መንገድ ነው።

💡አንደኛው መውጫ መንገድ ማኅበረሰቡን ከፕሮፓጋንዳ ማላቀቅ ነው። ወጣቱ ከጠባብ ብሔርተኝነት እና ከጦርነት ነጋዴዎች ፕሮፓጋንዳ ወጥቶ የሰላም እና የልማት ኀይል እንዲኾን ሥነልቦናዊ ግንባታ ላይ መሥራት ይገባል። በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ በመገንባት ወጣቶች ወደ ትምህርት ገበታቸው እና ወደ ሰላማዊ የሥራ እንቅስቃሴ እንዲመለሱ ማድረግም ሌላኛው መውጫ መንገድ ነው። ሕጋዊ ተጠያቂነትን ማረጋገጥም ተገቢ ነው። ወጣቱን ለጦርነት ማገዶነት የሚዳርጉ እና ለዳግም እልቂት የሚሠሩ ኀይሎችን በሕግ ፊት ተጠያቂ ማድረግም አስፈላጊ ነው።

በአጠቃላይ ሕገወጡ የሕወሃት ቡድን ወጣቱን ወዳልኾነ አቅጣጫ በመውሰድ ያደረሰው ታሪካዊ ስህተት እና አሁንም የሚታዩት ግትርነቶች የትግራይን ሕዝብ ብቻ ሳይኾን መላውን ኢትዮጵያ የሚጎዳ ነው። ሀገር ተረካቢው ትውልድ የጥፋት መሣሪያ መኾኑ አብቅቶ የሰላም እና የዕድገት ባለቤት ሊኾንም ይገባል። ሰላም!🕊

#አሚኮ_ዜና #ኢትዮጵያ🇪🇹 #ሰላም #በትግራይ #ወጣቶች #AMICO_News #The_Illegal_TPLF #Ethiopia🇪🇹

#ባሕር ዳር:ሐምሌ 05/2018 ዓ.ም

ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleየቤኒን ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ሮሙዋልድ ዋዳግኒ አዲስ አበባ ገቡ።
Next articleበሳዑዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ጉዳይ የተመለከተ መግለጫ