ከትላንት እስከ ዛሬ የማይደበዝዝ የጀግንነት እሴት🇪🇹

24

 

ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት የትላንት ታሪክ ኩራት፣ የቀደምት ትውልድ አሻራ፣ የዛሬ የሉአላዊነት ጋሻ፣ የብሔራዊ ክብር ሚዛን አስጠባቂ፣ የትውልድ ቅብብሎሽ ማሳያ፣ የሀገር ዘብ፤ ትናንትን ከዛሬ አዋህዶ ነገን አሻግሮ የሚያይ፣ የሀገር ተስፋ እና የሰላም ዋስትና ነው።💪

ታሪኩን ጠብቆ፣ ሕዝብን አክብሮ፣ ዳር ድንበርን አስከብሮ በጠንካራ መሠረት ላይ የተገነባ፣ ዛሬን በድል እየተወጣ ለነገው ትውልድ በጽናት የቆመ፤ የዘመን ተሻጋሪነት እና የአይበገሬነት ተምሳሌት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት።

ሠራዊቱ ሥርዓት ቢለዋወጥ፣ የጦርነት ስልቶች ቢቀያየሩ፣ ጠላቶች ቢበዙበት፣ በመሥዋትነት ለሀገር የመቆም ፅናት እና የጀግንነት እሴቱ የማይደበዝዝ የኢትዮጵያዊነት ደማቅ መልክ ኾኖ ዘልቋል።

ሀገር በተፈተነች ቁጥር ይበልጥ እየጎለበተ፣ ተዳክሟል ሲባል እየጠነከረ፣ አንሷል ሲባል እየገዘፈ፣ ተበተኗል ሲባል ይበልጥ እየተደራጀ የዘለቀው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሀገር ባለውለታ ብቻ ሳይኾን የብሔራዊ ኩራት እና የሀገር ምልክት ነው ።

በየዘመናት የሚገጥሙትን ፈተናዎች በድል እያለፈ የኢትዮጵያን ስም በዓለም አደባባይ በክብር አስጠርቷል፤ የዘመን ተሻጋሪነት አብነትም ኾኗል።

ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካውያንም ጋሻ መኾን የቻለ ኩሩ ሠራዊት ስለመኾኑም ተመስክሮለታል። በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎችን በብቃት በመወጣትም ዓለም አቀፍ ዝናን አትርፏል፤ ስሙን በወርቅ ቀለም አስፅፏል፤ ኢትዮጵያንም ከፍ ባለ የክብር ማማ አቁሟታል።

በኮሪያ፣ በኮንጎ፣ በሩዋንዳ፣ በቡሩንዲ፣ በላይቤሪያ፣ በደቡብ ሱዳን፣ በሱዳን እና በሶማሊያ ያከናወናቸው የሰላም ማሥከበር ተልዕኮዎች ለዚህ በማሳያነት የሚጠቀሱ ናቸው።

በተለያየ ወቅት የሚነሱ ኀይሎችን እየመከተ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እያረጋገጠ የግዛት አንድነቷን አስጠብቆ ከዚህ ዘመን ደርሷል።

በአሁኑ ወቅት የውስጥ እና የውጭ ኀይሎች ተቀናጅተው የሀገሪቱን ወቅታዊ የጸጥታ ውጥረት ተጠቅመው ለግጭት ቢንቀሳቀሱም ሠራዊቱ ግን ዛሬም ክንዱ አልዛለም።

ሠራዊቱ በውስጥ ግጭቶች እንዲወጠር በማድረግ የትኩረት አቅጣጫውን መከፋፈል በሚል የተሳሳተ እሳቤ ዓላማቸውን ለማስፈጸም እየተጣጣሩ እንደሚገኙም ይገለጻል።

ይህ የተሳሳተ ስሌት ህልም ኾኖ ይቀራል እንጂ ሊሳካ እንደማይችል የሠራዊቱን ወቅታዊ ቁመና በመተንተን የሀገሪቱ ከፍተኛ መሪዎች እና የሠራዊቱ አዛዦች ያረጋግጣሉ።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ያለጦርነት መኖር የማይችሉ፣ ባንዳነትን የተለማመዱ፣ ሽንፈት የማያሳፍራቸው፣ የኑሮ ዘይቤያቸውን ጦርነት ያደረጉ የጠላት መጠቀሚያ የኾኑ አካላት ለታሪካዊ ጠላቶቻችን እየተላላኩ ይገኛሉ ብለዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከሀገሪቱ ብሔራዊ ጥቅም በተጻራሪ የቆሙ ኀይሎችን አደብ ለማስገዛት በሚያስችል ሙሉ ቁመና ላይ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል።💯

የቀጣናውን አለመረጋጋት እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም የኢትዮጵያን ሰላም ለማወክ የሚጥሩ ኀይሎችንም በአርበኝነት ታሪካችን ላይ ተመሥርቶ የተገነባው ሠራዊታችን በየጊዜው መተንፈሻ እያሳጣቸው ይገኛል ነው ያሉት።

አሁን ላይ እግረኛን፣ ታንከኛን እና መድፈኛን በማሰለፍ መዋጋት ታሪክ እየኾነ ነው ያሉት ፊልድ ማርሻሉ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የጠላትን መሠረተ ልማት ማውደም የሚቻልበት ደረጃ ላይ ስለመደረሱም አስታውቀዋል።

ሠራዊቱ ሰው አልባ መሣሪያዎችን በመጠቀም ውጊያን በአጭር ጊዜ ማጠናቀቅ የሚያስችል ደረጃ ላይ መደረሱንም ጠቁመዋል።🛸

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከምንጊዜውም በላይ አንድነቱን ጠብቆ፣ አቅሙን አልቆ፣ የዘመኑን ቴክኖሎጂ ታጥቆ፣ አደረጃጀቱን አግዝፎ፣ ተደራሽነቱን አስፍቶ፣ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለመጠበቅ በከፍተኛ የዝግጁነት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።🚀💻

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ ቅንጣት ታክል ስጋት እንደማይኖር ተናግረዋል። ይህንንም ለማረጋገጥ የሚያስችል አቅም መገንባቱንም አረጋግጠዋል።

#አሚኮ #ኢትዮጵያ #የኢትዮጵያመከላከያሠራዊት #ENDF #EthiopianArmy #Ethiopia

#ባሕር_ዳር:ሐምሌ 06/2018 ዓ.ም

በአሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleሐምሌ 5 የወልቃይት ትንሳኤ ቁልፍ🔐!
Next articleየቤኒን ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ሮሙዋልድ ዋዳግኒ አዲስ አበባ ገቡ።